
በተለያዩ ምክንያቶች በእሥር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ክስ እንዲቋረጥ መንግሥት መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕረስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ የሰው ህይወት መጥፋት፣ ግጭት፣ መፈናቀል እና የሀይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት መከሰቱን ያወሱት የጽህፈት ቤት ኃላፊው በእነዚህ ሁኔታዎች መረጃ የተገኘባቸው 1 ሺህ 682 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሆነው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሙስናና በህገ ወጥ መንገድ ከማዘዋወር ጋር በተያያዘ ደግሞ 470 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ ብር ታግዶ ጉዳዩ እየታየ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ይሁን እንጂ በታጋሽነት እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ሲል የተወሰኑት ክስ እንዲቋረጥ መንግሥት መወሰኑን ነው አቶ ንጉሱ የተናገሩት። በዚህም መሠረት የ60 ሰዎች ክስ ማቋረጡን ገልጸዋል።
ክሳቸው የተቋረጠላቸው በየትኛው አግባብ፣ በምን ሁኔታ፣ እነማን እንደሆኑ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ነገ ማብራሪያ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።
በለውጡ ሂደት ብቻ 43 ሺህ 531 ዜጎች ምሕረት እንደተደረገላቸውም አቶ ንጉሱ አስታውሰዋል።
ፎቶ፦ ከፋይል