“ለበዓል ቤት ዘግተን እንውል ነበር፣ ድጋፍ ስለተደረገልን እናመሠግናለን” ድጋፍ የተደረገላቸው አካል ጉዳተኛ

10

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ድጋፍ አድርጓል፡፡
የበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ እናትትሁን ዓለም አካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት በዊልቸር በመታገዝ ነው፡፡ የአንድ ልጅ እናት ናቸው፡፡ እኒህ እናት ሳንቲም በማዘርዘር በሚያገኟት ገቢ ልጃቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ኑሯቸውንም ይመራሉ፡፡ የሚሠሩት ሥራ እና የኑሮ ውድነቱ አለመጣጣሙ ግን ኑሮውን አክብዶብኛል ይላሉ፡፡

በክፍለ ከተማው የሚደረግላቸው ድጋፍ የከበደውን ሕይወታቸውን እንደሚደጉምላቸውም ገልጸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ድጋፍ እየተደረገላቸውም የኑሮ ውድነቱ አስቸጋሪ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የሰላም እጦት ለእርሳቸው ከፈተና ላይ ሌላ ፈተና ጭኖባቸው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ የሰላም አለመኖር ለአካል ጉዳተኛ ከባድ ነው፣ ችግር ሲፈጠር ማምለጥ እንችልም፣ ልጆቻችንንም መሠብሠብ አይቻለንም ብለዋል፡፡

“ ለበዓል ቤት ዘግተን እንውል ነበር፣ ድጋፍ ስለተደረገልን እናመሠግናለን” ያሉት ወይዘሮ እናትሁን ዘላቂ ሰላም መጥቶ በሰላም እንዲኖሩ ሁሉም ለሰላም እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡
ወይዘሮ ዳሳሽ በሪሁንም የአካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴያቸው በዊልቸር ነው፡፡ ኑሯቸውን ሳንቲም በመዘርዘር እንደሚመሩ ነግረውናል፡፡ አሁን አሁን ሕመም እየጠናባቸው ሥራውን ለመሥራት መቸገራቸውን ነው የገለጹት፡፡ በበዓል ወቅት ሲገኝ እንቁላል ገዝተው፣ ሲታጣ ግን በቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን እንደሚያሳልፉ ነው የነገሩን፡፡ በዓልን ታሳቢ አድርገው ስላደረጉላቸው ድጋፍም አመሥግነዋል፡፡ አሁን ላይ ያለው የኑሮ ውድነት ለኖሯቸው ሌላ ጫና መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡

የሰላም እጦት ሲኖር መንገድ ይዘጋል፤ ድንጋይ ይጣላል፣ እኛ በዊልቸር ለመንቀሳቀስ እንቸገራለን፣ በዊልቸር ድንጋይ አልፎ መሄድ አይቻልምና፣ ለእኛ በጣም ከባድ ነው ብለዋል፡፡ ሁሉም ለሰላም በመቆም ችግራቸውን እንዲፈታላቸውም ጠይቀዋል፡፡

በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ የማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ግርማነሽ ተገኘ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ የተደረገው ድጋፍ ከማኅበረሰቡ የተገኘ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በዓልን ብቻ ጠብቀን ሳይኾን ሁሌም ድጋፍ ማድረግ ይገባል ያሉት ተወካይ ኀላፊዋ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ቋሚ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በዓል በመጣ ጊዜ ደግሞ ከቋሚ ድጋፍ ባሻገር ጊዜያዊ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ በክፍለ ከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ከ560 ሺህ ብር በላይ መሠብሠባቸውንም ገልጸዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ 658 ወገኖች ድጋፍ እንደተደረገላቸውም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በወገኖቻችን ላይ የተከሰተውን የድርቅ ጉዳት ለፖለቲካ ትርፍ ማዋል ከሰብአዊነት የራቀ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን
Next article”የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተሳታፊዎች ሠርተው እንዲለወጡ አስፈላጊውን እገዛ እናደርጋለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው