
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን የሚመራው የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ በክልሉ በተከሰተው የድርቅ አደጋ እና የድጋፍ ሥራዎች ላይ ግምገማ እና ውይይት አካሂዷል። በግምገማው ላይ ድርቁ ያለበትን ሁኔታ፣ ያደረሰው ጉዳት እና እየተደረጉ ያሉ የድጋፍ ሥራዎች ተነስተዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ድርቁ ያደረሰውን ጉዳት በተጨባጭ አጥንቶ መለየት እና መደገፍ ሲገባ ለፖለቲካ ፍላጎት ሲባል ኀላፊነት የጎደለው እና የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት ትክክል አለመኾኑን አስገንዝበዋል። “በወገኖቻችን ላይ የተከሰተውን ጉዳት ለፖለቲካ ትርፍ ማዋል ከሰብአዊነት የራቀ ተግባር ነው” ሲሉም ገልጸውታል።
የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር ድጋፎችን እያደረገ ስለመኾኑም ተናግረዋል። የተሠበሠበውን ሀብት አንቀሳቅሶ ለተጎጅዎች በማድረስ በኩል የጸጥታ ሁኔታው እንቅፋት እየፈጠረ መቆየቱንም ጠቁመዋል። ለወገን የሚያስብ ሁሉ ሰላሙን በመጠበቅ የተገኙ እርዳታዎች እንዲደርሱ አጋዥ መኾን አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል።
የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ግብረ ኃይል ሠብሣቢ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) የዛሬው ውይይት በተቋማት መካከል ቅንጅት ፈጥሮ ተጎጅዎችን ለመደገፍ እና በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን መንገድ ለማመቻቸት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ዶክተር ድረስ ከድርቁ ጋር በተያያዘ የሚፈጠረውን ርሃብ፣ የጤና ችግር፣ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እየተሠራ ሰለመኾኑም ተናግረዋል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ዋግኽምራ ሄደው የእርዳታ ስርጭቱን ስለመገምገማቸውም ገልጸዋል። ወደ ቦታው የደረሱ እርዳታዎችን በፍጥነት ወደተጠቃሚዎች በማድረስ በኩል ክፍተቶች ስለመኖራቸው በምልከታ ተረጋግጧል ብለዋል። ይህ ክፍተት ታርሟል፤ ቅንጅታዊ አሠራር ተፈጥሮ የተሠበሠበውን ሃብት ፈጥኖ ለተጎጅዎች የማድረስ ሥራም እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ዶክተር ድረስ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ከእርዳታ ፈጥነው እንዲወጡ እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ በአካባቢዎቹ ላይ የመስኖ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል። ለዚህም የክልሉ ግብርና ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመስኖ ሥራን የሚደግፉ የውኃ ፓንፖችን ያሰራጫል ብለዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም በችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን የመደገፍ ሥራውን ማገዝ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል ድርቁ በ9 ዞኖች፣ በ43 ወረዳዎች እና በ429 ቀበሌዎች ያዳረሰ፣ 1 ሚሊዮን 846 ሺህ 985 ሰዎችንም ለጉዳት ያጋለጠ ነው ብለዋል።
በተለይም ሰሜን ጎንደር እና ዋግኽምራ ላይ ድርቁ ሰፊ ጉዳት ማድረሱን ዲያቆን ተሥፋው ገልጸዋል። በሰዎች እና በእንስሳት ላይ ጭምር ርሃብ ማስከተሉን ጠቅሰዋል። ይህንን ጉዳት ለመቀነስ የክልሉ መንግሥት 430 ሚሊዮን ብር መድቦ እየተሠራ ነው ብለዋል። እስካሁንም 300 ሚሊዮኑ ወጭ ኾኖ ግዥ እየተፈጸመ እና ለተጠቃሚዎች እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የፌዴራል መንግሥትም በመጀመሪያው ዙር 120 ሺህ 800 ኩንታል የምግብ እሕል መድቧል፤ ከዚህም ውስጥ 70 በመቶው ተሰራጭቷል ብለዋል። ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ እየተጓጓዘ መኾኑን ጠቅሰዋል። ዲያቆን ተስፋው የተለያዩ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችም የእንስሳት መኖ ድጋፍ ከማቅረብ ጀምሮ ተጎጅዎችን ለመደገፍ ርብርብ እያደረጉ ነው ብለዋል።
እርዳታ አቁመው የቆዩ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ከሕዳር አጋማሽ ጀምሮ እርዳታ መጀመራቸው ጥሩ አጋጣሚ መኾኑንም አንስተዋል። ድጋፋ ለጊዜው ተሰጥቶ የሚቆም ሳይኾን ተጎጅዎች በዘላቂነት እስከሚቋቋሙ የሚቀጥል መኾን እንዳለበትም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል። ዛሬ የተደረገው ውይይት በአካባቢው የመስኖ ሥራ እንዲከናወን፣ የውኃ አቅርቦት እንዲሟላ፣ የተማሪዎች ምገባ እንዲጀመር እና ለተሟላ የጤና አገልግሎት ቅንጅት ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!