“በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ሊሸፈኑ ያልቻሉ ችግሮችን በመሸፈን በተቋቋምንበት ዓላማ ልክ በስፋት እንሠራለን” የኢትዮጵያ የኅብረት ሥራ ኮሚሽን

37

አዲስ አበባ: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ልማት እና እድገት የሪፎርም ንቅናቄ ማብሰሪያ መርሐ ግብር እያካሄደ ይገኛል። በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) የኅብረት ሥራ ማኅበራት በግብርናው ዘርፍ የማይተካ ሚና ተወጥተዋል ብለዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራት በዓመት 6 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ተገኝቶ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንድትኾን አስችሏል፤ የግለሰቦችን አቅም በማሰባሰብ እና የቴክኖሎጂ አቅም በማስታጠቅ ሚናቸው የበዛ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ.ር) ኅብረት ሥራ ማኅበራት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ሊሸፈኑ ያልቻሉ ችግሮችን በመሸፈን በተቋቋምንበት ዓላማ ልክ በስፋት እንሠራለን ብለዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ወሳኝ በመኾናቸው ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና የሕዝቡን ችግር ለመቅረፍ በስፋት እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፤ ይሕም ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የገንዘብ ብድር እና ቁጠባዎችን በማመቻቸት፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ ከተማ እና ገጠሩን ያገናኘ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማቅረብ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ሚና የተወጡ መኾናቸው በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ የገበያ እድል በማመቻቸትም ሚናቸውን መወጣታቸውም ተነስቷል፡፡ ማኅበራቱ የእሁድ ገበያዎችን በማመቻቸት እና መሰል የገበያ መረጋጋት እና የምርት ተደራሽነት ላይ በስፋት በመሥራት ማኅበረሰቡን በችግሩ ላይ እያገለገሉ ነው ተብሏል።

እስካሁን በተከናወነው ተግባር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠራቸው ተገልጿል። ማኅበራቱ ከዚህ በላይ አቅም እና አደረጃጀታቸው ሰፍቶ ማኅበረሰቡን ማገልገል እንዲችሉ በስፋት ይሠራል ተብሏል። አሁን ካለው የማኅበራቱ አደረጃጀት ባሻገር የኅብረት ሥራ ባንክ እንዲቋቋም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በስፋት እንደሚሠራም ኮሚሽነሩ ዶክተር ጌታቸው መለሰ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው እባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዘንድሮ ከ2 ቢልየን በላይ ቡና፣ ከግማሽ ቢልየን በላይ ፍራፍሬ እና ከ400 ሚልየን በላይ የሻይ ተክል ዝግጅት ተጀምሯል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“በወገኖቻችን ላይ የተከሰተውን የድርቅ ጉዳት ለፖለቲካ ትርፍ ማዋል ከሰብአዊነት የራቀ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን