
በጫካ የሚገኙ ወንድሞች የሰላም ጥሪዉን በመቀበል ለክልሉ ሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡ በማለት የሰላም ጥሪውን የተቀብሉ ወጣቶች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ደሴ: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጫካ የሚገኙ ወንድሞች የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለክልሉ ሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡ በሰሜን ወሎ ዞን የሰላም ጥሪውን የተቀብሉ ወጣቶች አሳስበዋል፡፡
የሰላም ጥሪውን የተቀብሉ ወጣቶች የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በሰሜን ወሎ ዞን ብቻ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ክልሉ በተለይ ባለፉት 3 ዓመታት ሰላሙ ደፍርሶ ሕዝቡ ለበርካታ ችግሮች ተጋልጧል፤ ከዚህ በላይ በግጭት ውስጥ መቆየት ተጨማሪ ጥፋትን መጋበዝ በመኾኑ ሰላማዊ አማራጭን መርጠናልም ብለዋል፡፡
የመንግሥት ጥሪ ተቀብለው ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ከገቡ ጀምሮ ሰብአዊ ክብራቸዉ ተጠብቆ ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙም ነዉ የተናገሩት፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ሻምበል ቢሰጥ በክልሉ ላይ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ያጋጠመዉን የሰላም መደፍረስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባደረገው የሰላም ጥሪ በርካታች የሰላም ጥሪዉን ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሻምበል በዞኑ ከ170 በላይ ታጣቂዎች የክልሉን የሰላም ጥሪ ተቀብለዉ እንደገቡም አንስተዋል፡፡ ሰላማዊ የትግል አማራጭን በመምረጥ የገቡ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ያደረገዉ የሰላም ጥሪ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል ያሉት የመምሪያ ኀላፊዉ አሁን የሰላም ጥሪዉን የሚመርጡ ታጣቂዎችን እየተቀበሉ ሥልጠና እየሠጡ ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ ነዉ የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!