
ባሕርዳር: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተካሄደው ይፋዊ የአቀባበል መርሐ ግብር ላይም የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በሦስት ዙር የሚካሄደው ‘ወደ መሰረት መመለስ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪን ተከትሎ ከተለያዩ ሀገራት ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት በመግባት ላይ መኾናቸውን ከኢትዮጵያ የዳያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ጥሪ ከታኅሳሥ 20 እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ የሚቆይ ነው፤ ‘ከብዝኃ ባህል መሰረትዎ ጋር ይገናኙ’ በሚል መሪ መልዕክት ስር የሚካሄድ ይሆናል።
በጥሪው ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የእረፍት ጊዚያቸውን ተጠቅመው የትውልድ ሀገራቸውን ባሕሎችና ትውፊቶች እንዲገነዘቡ እንዲሁም ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ትስስር እንዲፈጥሩ በሚያስችሏቸው ሁነቶች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ወደ መኖሪያ ሀገራቸው ሲመለሱ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ አምባሳደሮች እንዲኾኑ የማስቻል ዓላማን የሰነቀ መኾኑ ተገልጿል።
ጥሪውን ተቀብለው ለሚመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች የዋጋ ቅናሽ አድርገው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸው መገለጹ ይታወቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!