
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጪው የልደት በዓል ወቅት ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በበዓሉ ዕለት ሊያጋጥም የሚችለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ለመቀነስ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጿል።
በበዓሉ ዋዜማም ኾነ በዕለቱ የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ሳይፈጠር ለተጠቃሚው ለማቅረብ እና ችግሮች ከተከሰቱም በአፋጣኝ አስቸኳይ ጥገና ለማከናወን የሚያስችል በየደረጃው ግብረ-ኀይል በማዋቀርና አስፈላጊ የኾኑ ግብዓቶችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱን አገልግሎቱ አስታውቋል ፡፡
የሚመለከታቸው አካላት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመቀናጀትና የጋራ ግብረ ኀይል በማዋቀር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በጋራ መሠራታቸውንም አስታውቋል። በተደጋጋሚ ችግር የሚስተዋልባቸውን መስመሮች በመለየት የቅድመ መከላከል ጥገና ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ አመላክቷል፡፡
ደንበኞች የኃይል አጠቃቀማቸው ለአደጋ ተጋላጭ እንዳያደርጋቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው በማስታወስ የኃይል ጭነት በማይበዛባቸው ሰዓታት በተለይ ከምሽቱ 3፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባሉት ጊዚያት መጠቀም የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማግኘት ባለፈ ሊኖር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስገንዝቧል።
የበዓል ወቅት ከመኾኑ ጋር በተያያዘ የታደሰ የተቋሙ መታወቂያና የሥራ ትእዛዝ ደብዳቤ የያዙ የቴክኒክ ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለሥራ ጉዳይ እንደሚንቀሳቀሱ ገልጿል።
የተቋሙ ሠራተኞችን በመምሰል መሠረተ ልማቱ ላይ ስርቆትና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ ኅብረተሰቡ ይህንን ከወዲሁ ተገንዝቦ የኤሌክትሪክ መሰረት ልማቶችን እንዲጠበቅና አጠራጣሪ ነገር ካጋጠመው ለፀጥታ አካላት ወይም ለተቋሙ ጥቆማ እንዲሰጥ አገልግሎቱ ጠይቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
