
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሃይማኖቶች የመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ዕሴት መሠረቶች በመሆን ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባርና የግብረ ገብነት ትምህርትና ግንባታ የሚከናወንባቸው ማዕከላት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሃይማኖታዊ ትዕዛዛትና አስተምህሮዎችም የሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነትና ቁርኝነትን በማጠናከር ሰላም፣ መከባበር፣ አብሮነት፣ ይቅርታ፣ እርቅ፣ ፍትሕ እና የመሳሰሉ በጎ ዕሴቶችን በማስተማር ዘመናትን የዘለቀ አገልገሎት ሲሠጡ ኑረዋል፤ እየሠጡም ይገኛሉ ብሏል በመግለጫው፡፡ ይህም ሀገራዊ አንድነትን አስጠብቆ ለመዝለቅ ማስቻሉን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታውቋል።
ከዚህም ባለፈ የሃይማኖት አባቶች ዋና ተልዕኳቸውና አገልግሎታቸው የሰው ሁለንተና ማገልገልና አማኞች ፈሪሀ ፈጣሪ አድሮባቸው የመንፈሳዊ ልዕልና እንዲጎናፀፉ ማድረግ ሲሆን ለዚህም ራሳቸውን ከዓለማዊ ጉዳዮችና ጣጣዎች በመራቅ እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት በምሳሌነት እየኖሩ አስተምህሮው የሚያዛቸውን በተግባር ገልጠዋል ብሏል በመግለጫው፡፡
ጉባኤው በመግለጫው እንዳስታወቀው የሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነትና መስተጋብርም የሰመረ እንዲኾን መንፈሳዊ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በማስተማር፣ በመምከርና በመገሠፅ የአባትነት፣ የጠባቂነትና የመሪነት አደራቸውንና ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፤ እየተወጡም ይገኛሉ፡፡ በተለይም በመንግሥታዊም ይሁን መንግሥታዊ ባልኾኑ ተቋማት የሚስተዋሉ በደሎችንና ኢፍትሐዊነቶች ሁሉ እንዲታረሙና እንዲስተካከሉ መጣር፣ አጥፊዎችም ከስህተታቸው እንዲታረሙ በፍቅር መገሰፅ ሃይማኖታዊና የተለመደ አሠራር በመኾኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስቧል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ከዚህ መሠረታዊ ተልዕኮና ዓላማ በማይስማማ አኳኋን ለሃይማኖታዊ ተግባርና ዓላማ በሚደረጉ ስብስቦች እና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ተገቢ ያልሆኑና በአብዛኛው ፖለቲካዊ ይዘት የጎላባቸው፣ ሀገር አፍራሽና ደም አፋሳሽ ስብከቶችና ትንታኔዎች ሲነገሩ ተመልክተናል ነው ያለው፡፡ ስብከቶቹና ንግግሮቹ ፖለቲካውና ፖለቲከኞችን የሚተቹ ወይም የሚደግፉ ከመሆናቸው በላይ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ የመቀስቀስና የማነሳሳት አዝማሚያ የሚታይባቸው መኾኑ ጉዳዩ ከየትኛው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር የማይስማማና ድጋፍም የሌለው መኾኑ ደግሞ የስብከት ልምምዱ አደገኛና በእጅጉ የሚወገዝ መኾኑም ተገልጿል።
እንዲህ ዓይነቱ ስብከትና አካሄድም የሰላም፣ የመከባበርና የአብሮነት ዕሴቱን የሚጎዳ በመኾኑ በአፋጣኝ ሊታረም ይገባል፤ የሃይማኖት ተቋማትም እንዲህ ዓይነት ስብከት የሚሠብኩና የሚናገሩ አባቶችን፣ አስተማሪዎችን ወይም ሰባኪ አገልገዮችን እንዲታረሙ የማድረግ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መንፈሳዊ ልዕልናን እንዲያሰፍኑ ጭምር ጉባኤያችን በአጽንኦት ያሳስባል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ብሏል በመግለጫው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!