
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያናት ካውንስል የልደት በዓልን አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት “ኢትዮጵያውያን ከሞራል ዝቅጠት በአስቸኳይ መውጣት አለባቸው” ብለዋል፡፡
ጠቡ መለያየቱ መጨካከኑ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት ኾኖም ያተረፍነው ውድመት ብቻ ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ “እርቅ እና ይቅርታ ማንን ጎዳ ሰላም እና አንድነት ማንን አከሰረ” በሰበብ አስባብ እየተፈላለጉ ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት ብለን በእኩልነት እና በስምምነት አንኖርም ብለዋል፡፡
የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ልሂቃን ተግተን ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዚህ የበኩላቸውን ድጋፍ ያድርጉ ሲሉም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳስበዋል፡፡ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በተዋበ እና ምቹ በኾነ የሀብታም ቤት ሳይኾን በከብቶች በረት ነበር” ነው ያሉት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ለጻድቃን ሳይኾን ለኃጢያተኞች መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ለድሆች እና ለጦም አዳሪዎች ትኩረት መሥጠት ይገባል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ እና ችግር ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ወገኖች የወገን ደራሽ ወገን ነው እና ሁሉም ካለው ብቻ ሳይኾን የቁርሱን ለተቸገሩ ወገኖች በመለገስ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በበኩላቸው ከመገዳደል ወጥተን ችግራችንን በውይይት የመፍታት ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች በእውነት እና በቅንነት ተመካከረን ችግሮች እንዲፈቱ ማሳሰብ ይገባናል ነው ያሉት፡፡ ቄስ ደረጄ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርስ ከመጠቋቆም እና ከመወነጃጀል ወጥቶ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ኀላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
በዘር በቋንቋ በነገድ በሃይማኖት ተለያይተን ለመጠፋፋት ከመሞከር ይልቅ ለሀገር የሰላም ግንባታ የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ መረባረብ ይገባናል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!