የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የመምህራን መኖሪያ ቤት እየገነባ መኾኑን አስታወቀ።

15

ደሴ: ታኅሳሥ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመኖሪያ ቤት ግንባታው ተረጋግቶ ለማስተማር እና የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚያስችል የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቱሉ አውሊያ ግቢ መምህር ዶክተር ዋለ ተስፋዬ እና አቶ መሰረት አበበ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ያለበት አካባቢ በቂና ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት የማይገኝበት በመኾኑ በችግር ላይ ቆይተዋል።

የመምህራን መኖሪያ ቤቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ መምህራን በተረጋጋ መንፈስ ለመሥራት ያስችላቸዋል ነው ያሉት። የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስለሽ አቢ ዩኒቨርሲቲው ከከተማ ርቆ የተመሠረተ በመኾኑ መምህራን የሚከራዩት ቤት ለማግኘት ሲቸገሩ ቆይተዋል ብለዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው በሁለቱም ግቢዎች የመምህራን ቤት ግንባታ እያካሄደ እንደኾነም አስረድተዋል። የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰዋአገኝ አስራት ዩኒቨርሲቲው በሁለቱም ግቢዎች አራት ብሎኮች እያንዳንዳቸው 126 የመኖሪያ ቤቶችን የያዙ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ በመገንባት ላይ ነው ብለዋል።

ግንባታውን በተያዘለት ግዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ የበጀት እጥረት እንዳያጋጥም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡትም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡- ሰይድ አብዱ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ የኢሜግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡
Next article“የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ልሂቃን ተግተን ለሰላም ልንሠራ ይገባል” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ