በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ የኢሜግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡

27

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢሜግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ከጥር 1/2016 ዓ.ም እስከ ጥር 30/2016 ዓ.ም ድረስ ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢሜግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖራቸውን ያህል በሀሰተኛ ሰነዶች የሚኖሩ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በተደረገው ማጣራትም ከ18 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ሀሰተኛ የመኖሪያ ፈቃድ እና ከ1ሺህ 500 በላይ ደግሞ ሀሰተኛ ቪዛ ይዘዉ መገኘታቸውን ገልጸዋል። በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ በመኾናቸው ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በሀሰተኛ ሰነዶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ከጥር 1/2016 ዓ.ም እስከ ጥር 30/2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ተቋሙ ቀርበው ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡም በመግለጫው ጥሪ ቀርቧል። ይሄን በማያደርጉ የውጭ ዜጎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ዋና ዳይሬክተሯ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለልደት እና ጥምቀት በዓላት በአማራ ክልል ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እንደሚሰራጭ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
Next articleየመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የመምህራን መኖሪያ ቤት እየገነባ መኾኑን አስታወቀ።