
ባሕርዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዘጠነኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።9ሰዓት ባሕርዳር ከተማ ከሻሼመኔ ከተማ ጋር ይጫወታል።
የጣና ሞገዶቹ በስምንት ጨዋታዎች 17 ነጥቦችን ሰብስበዋል።በደረጃ ሰንጠረዡም ከንግድ ባንክና መቻል ቀጥሎ ተቀምጧል። ሻሼመኔ ከተማዎች የፕሪሜየር ሊግ ጉዟቸው ፈተና የበዛበት ነው።እስካሁን ሦስት ነጥብ ማግኘት አልቻሉም።በስምንት ሳምንት የፕሪሜየር ሊጉ ጉዞ ያሳኩትም ሁለት ነጥብ ብቻ ነው።በሰንጠረዡ 15ተኛ ላይ ናቸው።
በዛሬው ጨዋታ ባሕርዳሮች አሸንፈው ይበልጥ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመኾን ይጫወታሉ።ሻሼመኔዎች ደግሞ በፕሪሜየር ሊጉ ለመቆየት ነገሮችን ለመቀየር ይህን ጨዋታ መነሻ ለማድረግ የቻሉትን ያደርጋሉ።
ጨዋታው 9ሰዓት የሚጀምር ሲኾን በጣና ሞገዶቹ በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ስለመኾናቸው ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል። ሌላኛው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስና መቻል መካከል ምሽት 12ሰዓት ይካሄዳል።ሁለቱ ቡድኖች ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው በመኾኑ ጨዋታው ተጠባቂ ነው።
ፈረሰኞቹ በ16 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፤በዚህ ዓመት በብዙ የተሻሻለው መቻልም 19 ነጥብ ይዞ በሊጉ በንግድ ባንክ ብቻ ነው የሚበለጠው። ፈረሰኞቹ በሸገር ደርቢ በተስተካካይ ጨዋታ ከተሸነፉ በኃላ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።በመኾኑም ከሽንፈት ለማገገም በጨዋታው ድል ማድረግን አጥብቀው ይፈልጉታል።በተጨማሪም በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ከተቀመጡ ቡድኖች በነጥብ ላለመራቅ ጨዋታውን ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል።
መቻሎችም የተሻለው የፕሪሜየር ሊግ ጉዞቸውን ለማስቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻሉም ለጊዜውም ቢኾን የደረጃ ሰንጠረዡን መምራት ይችላሉ።
አስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!