
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝቡ በፍትሕ ሥራዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረውና ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ በፍትሕ ጥራት ላይ መሥራት እንደሚገባ ነው አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ያሳሰቡት። በሀረሪ ክልል ሀረር ከተማ የተካሄደው የሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የምክክር መድረክ ተጠናቅቋል።
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት፤ ኅብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ጥራት ላይ የሚነሳውን ችግር ለመቅረፍ የፍትሕ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኀብረተሰቡ የፍትሕ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት እምነት ኖሮት ወደ ፍትሕ ተቋማት እንዲመጣ ለማድረግ የፍትሕ ተቋማቱ በቴክኖሎጂ የተደግፈው ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸው መኾኑን አመላክተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በሰጡት አስተያየት፤ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ ያለው ትራንስፎርሜሽን ወደ ኋላ እንዳይመለስና ውጤታማ እንዲኾን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ሎሚ በዶ በፍትሕ አካላት ላይ የሚነሳው የፍትሕ ችግር ብቻ አይደለም ብለዋል፡፡ ምክትል አፈጉባኤ ሎሚ የሚታየውን የመልካም አሥተዳደር፣ የሰላም እና የፀጥታ ችግርን ለመቅረፍ የፍትህ ጥራትን ማስጠበቅ ይገባል፤ ለዚህም ከወረዳ እስከ ፌዴራል በሚሠራው ትራንስፎርሜሽን ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አንድ ተቋምን በማጠናከር ብቻ የፍትሕ ሥርዓቱን ማሻሻል ስለማይችል ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ የፍትሕ አካላት ተቀናጅተው በመሥራት የተጀመረውን ትራንስፎርሜሽን ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) በሰጡት አስተያየት ኅብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ እምነት እንዲኖረው በየደረጃው ባሉ የፍትሕ አካላት የትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ መሪዎች ትብብር እንዲያደርጉና እንዲያስተባብሩ የክልል አፈ ጉባኤዎችን ጠይቀዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት በዳኝነት በኩል ያለውን የሕዝብ እሮሮ ለማስቀረት የዳኝነት ነፃነትን በማይነካ መልኩ የፍትሕ ጥራትን ለማሻሻል በትብብር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ እፀገነት መንግሥቱ በኅብረተሰቡ የተፈጠረው ንቃተ ሕግ ኅብረተሰቡ መብቱን ለማስጠበቅ እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲሟገት አስችሎታል ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ የሕግ ስህተት አለ ብሎ ሲያስብም እስከ ሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመምጣት እየተከራከረ መብቱን ለማስጠበቅ ልምምድ እያደረገ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው በየደረጃው ያሉ የፍትሕ አካላትም የፍትሕ ጥራትን ለማስጠበቅ ጥሩ ተሞክሮ ካላቸው የፍትሕ አካላት ተሞክሮ መውሳድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!