የሰሊጥ ምርት ግብይትን ከሕጋዊ ሥርዓቱ ውጪ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት በሚሠሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ።

20

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ ሰሊጥ አምራች ከኾኑ አካባቢዎች ውስጥ የአማራ ክልል ተጠቃሽ ነው። በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ሰቲት ሁመራ ወልቃይት ጠገዴ፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሊጥ አምራች ከኾኑት አካባቢዎች ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው።
ምዕራብ ጎንደር ዞን ደግሞ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በዞኑ በ2015/16 የምርት ዘመን በስፋት ከተመረቱ ገበያ ተኮር ምርቶች ውስጥ ሰሊጥ ይገኝበታል።

በምርት ዘመኑ በአካባቢው ከፍተኛ የሰሊጥ ምርት ቢያመርቱም አምራቾች በሚፈልጉት ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሸጡ መገደቡን እና በነጋዴው በኩል የዋጋ ልዩነት መኖሩን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ነግረውናል።

አርሶ አደር አየልኝ ሀብቴ በመተማ ወረዳ ደለሎ እየተባለው በሚጠራው አካባቢ በዘርፉ ተሰማርተዋል፡፡ 400 ሄክታር መሬት ላይ የሰሊጥ፣ የጥጥ፣ የአኩሪ አተር እና የማሽላ ሰብሎችን አምርተዋል፡፡

አርሶ አደር አየልኝ 500 ኩንታል የሰሊጥ ምርት አግኝተዋል፡፡ አርሶ አደሩ ያመረቱትን ምርት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች አጓጉዘው በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ቢፈልጉም እንዳልተፈቀደላቸው ነግረውናል፡፡

አርሶ አደር አየልኝ “የዋጋ ተመኑ በባለሃብቶች ስለሚተመን ኪሳራ አጋጥሞናል” ብለዋል። በቀጣይ አምራቾች ከፈለገው ቦታ የመሸጥ መብት ሊረጋገጥ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የሰብል ግብይት ባለሙያ ያረጋል ዳምጤ እንዳሉት ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዚህ በፊት ዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋን መሠረት አድርጎ ያወጣው የነበረው የዋጋ ተመን የገበያ ጣልቃ ገብነት ያለው ኾኖ በመገኘቱ ከዚህ ወር ጀምሮ በነፃ ግብይት እንዲፈጸም ተደርጓል ብለዋል።

የነጻ ግብይቱ ሕጋዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከናወን ተቋሙ የራሱ አሠራር እንዳለው ገልጸዋል። የግብይት ሥርዓቱን የሚያውክ አካሄድ ከተገኘም ከአሥተዳደራዊ እርምጃ ባለፈ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

የአስገዳጅ ምርቶች ግብይትን በተመለከተ አምራቾች ከአካባቢያቸው ውጭ በሚገኝ የግብይት ማዕከል ግብይት መፈጸም እንደማይችሉ በተሻሻለው መመሪያ 929/2015 ላይ መቀመጡን ገልጸዋል። ይህ ማለት አምራቾች በአካባቢያቸው በሚገኝ አንደኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል ለሚገኙ ላኪዎች፣ አቀነባባሪዎች፣ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኔኖች መሸጥ እንዳለባቸው ያስቀምጣል።

ነጋዴዎችም የግብይት ሥርዓቱን በሚረብሽ መንገድ ዋጋን ተስማምተው ግብይት እንዳይፈጽሙ የሸማቾች አዋጅ ቁጥር 813 ላይ መቀመጡን ገልጸዋል። ቢሮውም በተቀመጠው መመሪያ መሠረት አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት በሚሠሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት መሰራጨቱን አስታወቀ።
Next article“የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር የተቸገሩትን ሁሉ በመልካም ተግባር በማሰብ ይሁን” የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን