የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት መሰራጨቱን አስታወቀ።

20

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለመማር ማስተማር ተግባሩ የሚረዱ 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን መጽሐፍትን ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን መጻሕፍት ለአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሰራጨቱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 918 ሺህ 76 መጻሕፍት ተሰራጭቷል ብለዋል። 3 ሚሊዮን የሚኾነውን መጻሕፍት በክልሉ ባለው የጸጥታ ኹኔታ የተነሳ ማሰራጨት አለመቻሉን ጠቁመዋል።

ለአንደኛ ደረጃ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚኾኑ መጻሕፍት ከውጭ ታትመው የገቡ መኾኑን ገልጸዋል። በመጋዘን የተቀመጡትን በማከፋፈል ለመማር ማስተማር ተግባሩ እንዲውሉ ይደረጋልም ብለዋል።

በክልሉ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመቀበል ታቅዶ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚኾኑትን መመዝገብ የተቻለ ሲሆን ቀሪዎቹን ደግሞ በተቀናጀ መልኩ ለማስጀመር እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በተያያዘ በክልሉ 75 ሚሊዮን ብር በመመደብ የትምህርት ቤቶች ምገባ ሥርዓት እየተካሄደ መኾኑ ተገልጿል። በክልሉ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመገብ ታቅዶ ወደ ተግባር ቢገባም እስካሁን 200 ሺህ የሚኾኑት ብቻ ተጠቃሚ መኾናቸውን ምክትል ኀላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ተወዳዳሪ የኾነ ትውልድ ለማፍራት እንዲቻል አስፈላጊ የሆነውን የትምህርት ቤት ምገባ በታቀደው ልክ እንዳይፈጸም የተለያዩ እንቅፋቶች ማጋጠማቸውን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመትም 844 ሺህ ጎልማሶችን ለማስተማር ታቅዶ በተሠራው ሥራ መፈጸም የተቻለው 28 በመቶ ብቻ መሆኑን ነው የተናገሩት። በየዓመቱ ዕቅድ ታቅዶ ወደ ተግባር ቢገባም እስካሁን ግን አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል።

የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቅጥር አለመፈጸም፣ የቅንጅት አለመኖር እና ጥብቅ ክትትል አለማድረግ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መኾን እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ሰነድ ተዘጋጅቶ ከአጋር አካላት ጋር በጥምረት እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል ሲል ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተከሰተውን “ጉንፋን መሰል” ሕመም እንዴት መከላከል ይቻላል?
Next articleየሰሊጥ ምርት ግብይትን ከሕጋዊ ሥርዓቱ ውጪ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት በሚሠሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ።