የገና እና የጥምቀት በዓላትን በተሳካ ሁኔታ እና በሰላም ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

21

ጎንደር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የገና እና የጥምቀት በዓላት በተሳካ ሁኔታ እና በሰላም ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገልጿል። የከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የጸጥታ ኃይሎች ለበዓላት እየተደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት ገምግመዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን እና ወትሯዊ ድምቀቱን ጠብቆ እንዲከበር ሁሉም አካለት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መኾኑን ከንቲባው ተናግረዋል ። የባለፈው ዓመት ጥምቀት ለቱሪዝም ፍስሰቱና ለኢኮኖሚው መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ያስታወሱት ከንቲባው ዘንድሮም ካለፈው ዓመት በተሻለ እንዲከበር ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።

በዓሉን ለማክበር ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን በሰላም ተቀብሎ በሰላም ለመሸኘት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ከንቲባው ተናግረዋል ። የከተማው ሕዝብ፣ የእምነቱ ተከታዮች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የበዓሉ ባለቤት በመኾናቸው በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን እንደሚሠሩም ከንቲባው ገልጸዋል ።

ወደ ከተማዋ ለሚመጡ አዳዲስ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እና የቦታ አቅርቦት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋ። ወደ ጎንደር የሚመጡ እንግዶች የምኝታ አገልግሎት ችግር እንደማይገጥማቸው የገለጹት ከንቲበው ከሆቴሎች በተጨማሪ መላው ማኅበረሰብ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መኾኑን አቶ ባዩህ ተናግረዋል ።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አሰፋ አሸቤ እስከቀበሌ ድረስ የተቀናጀ የጸጥታ ማስከበር አሠራር መዋቀሩን ተናግረዋል። በዓላቱ የጎንደር ከተማን ቱሪዝምና ኢኮኖሚ የሚያነቃቁ በመኾናቸው ማኅበረሰቡ ለሰላሙ የራሡን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:- ተስፋዬ አይጠገብ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት በቀጣናው ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚፈጥር መኾኑ ተገለጸ።
Next articleየተከሰተውን “ጉንፋን መሰል” ሕመም እንዴት መከላከል ይቻላል?