
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት በቀጣናው ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚፈጥር መኾኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን በርበራ ወደብን ለረጅም ጊዜ መጠቀም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ ለተቋማቸው አመራሮችና ሠራተኞች ገለጻ አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንደገለጹት ሥምምነቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በጋራ እንዲለሙ ከማድረጉም በላይ በቀጣናው ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር በመፍጠር ሂደት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የጀመረችው ኢኮኖያዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋ። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የሚሄድ በመኾኑ ይህን የሚያስተናግድ የወደብና የሎጂስቲክ ግንኙነት ከጅቡቲ፣ ከኬንያና ከሌሎችም ሀገራት ጋር እንደሚቀጥልና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እየዳበረ እንደሚሄድ አመላክተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሕጋዊ መንገድ የወደብ ባለቤትና ተጠቃሚ መኾናችን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይኾን ሁለንተናዊ ጥቅም ያለው በመሆኑ ታላቅ ሀገራዊ ድል ነው ብለዋል፡፡
የሚኒስቴሩ ሠራተኞችም ለረጅም ጊዜ በቁጭትና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ሀገራዊ አጀንዳ እውን መኾኑ እንዳስደሰታቸው መግለጻቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!