“ሀገር ሰላም የሚኾነው ጣት ከመቀሳሰር ወጥቶ በአንድነት መሥራት ሲቻል ነው” የአማራ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

38

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት የጋራ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የጋራ ምክር ቤቱ ሠብሣቢ ተስፋሁን ዓለምነህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በክልሉ ወቅታዊ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በውይይቱ በክልሉ አሁናዊ የሰላም ኹኔታ፣ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎች እና የአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ከሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ጋር የጋራ ስምምነት ስለደረሰበት ኹኔታ ተወያይቷል ነው ያሉት።

የሰላም ስምምነቱን ምክር ቤቱ እንደመልካም ተሞክሮ ይወስደዋል ብለዋል። ማንኛውንም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናልም ነው ያሉት። “ሀገር ሰላም የሚኾነው ጣት ከመቀሳሰር ወጥቶ በአንድነት መሥራት ሲቻል ነውም” ብለዋል። “ሁላችንም ለሰላም አስተዋጽኦ ለማድረግ በመግባባት ተስማምተናል” ብለዋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሀገራዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት ተስፋ ተጥሎበታል ያሉት ሠብሣቢው በነቃ መንገድ ለመሳተፍ እና ፍትሐዊነት እንዲኖር በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል። የጋራ ምክር ቤቱ የሕዝብ ጥያቄዎች በተሟላ መንገድ እንዲቀርቡ እና የተሳታፊ ልየታ እንዲደረግ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ሰላምን ማዕከል ያደረገ ውይይት ከታጣቂ ኀይሎች ጋር ማድረጉ የሚበረታታ እና በጋራ ምክር ቤቱ ተቀባይነት ያለው መኾኑንም ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አባል ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የክልሉን ወቅታዊ ኹኔታ በጥልቀት ገምግመናል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ሰላምን ለማምጣት የሠራውን ሥራ መገምገማቸውንም አንስተዋል። በክልሉ የተፈጠረውን ቀውስ ለመቀልበስ የተሠራውን ሥራ መገምገማቸውንም ገልጸዋል። ቀውሱ ከተቀለበሰ በኋላ በክልሉ ሕዝብን የማረጋጋት ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል። “በክልሉ የታየው ሰላም የፀና እንዲኾን መደረግ በሚገባው ጉዳይ ላይም መክረናል” ነው ያሉት።

የክልሉን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የክልሉን የፀጥታ መዋቅር ማጠናከር እና መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ እንደሚገባ የጋራ ስምምነት መድረሳቸውን አብራርተዋል። ሕዝቡ ሰላማዊ ኾኖ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ መሥራት እንደሚገባም ስለመግባባታቸው ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ ያሉት ጥያቄዎች እንዲፈቱ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቂ እና የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው መስማማታቸውን ገልጸዋል። ውይይቱ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስም ይቀጥላል ተብሏል። የክልሉን ሰላም ለማጽናት ወጥ የኾነ አቋም መያዝ እንደሚገባም ነው ያስረዱት።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ሊፈታ የሚችለው በምክክር፣ በውይይት እና ከሌሎች ጋራ በመግባባት መኾኑን ነው ያስረዱት። ለምክከር ኮሚሽን የሚቀርቡ ተሳታፊዎችን እና አጀንዳዎችን ለመለየት በጋራ መሥራት እንደሚገባ መግባባታቸውንም ገልጸዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ የሚያመጣውን እድል መጠቀም እንደሚገባ በጥልቀት መምከራቸውንም አንስተዋል። ከውይይት እና ከሰላም የዘለለ የሚደረጉ አካሄዶች የአማራን ሕዝብ ያሳንሰው ካልኾነ በስተቀር ጥያቄውን አይፈታውም ተብሏል። የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመፍታትና የፀና ሰላም እንዲኖር ለማድረግ በጋራ መሥራት ከሁሉም እንደሚጠበቅ በመግለጫው ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዘላቂ አብሮነትን ለመገንባት አሰባሳቢ ትርክትን ማጎልበት ይገባል” አቶ አደም ፋራህ
Next articleየኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት በቀጣናው ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚፈጥር መኾኑ ተገለጸ።