
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአብሮነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ “ብዝኀነትን መኖር!” በሚል መሪ ሀሳብ ከታኅሳሥ 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል። ቀኑን ምክንያት በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የተሳተፉበት የስፖርት መርሐ ግብር በተለያዩ አካባቢዎች ተካሂዷል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤትም “አብሮነትን ለማጠናከር የሚተጋ አመራር” በሚል መሪ ሀሳብ ማኅብረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴ መርሐ ግብሩ ተከናውኗል።
በመድረኩ መልእክት ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኀላፊው አደም ፋራህ መርሐ ግብሩ ስፖርት ለአብሮነት መጠናከር ጉልህ ሚና ያለው በመኾኑ ግንዛቤ ለመፍጠር ጭምር ነው ብለዋል።
አቶ አደም “አብሮነትን በዘላቂነት ለመገንባት አሰባሳቢ ትርክትን ማጎልበት ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል። ድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ ግጭትና መሰል ችግሮችን ለመሻገር ብዝኀነትን ያማከለ አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በአብሮነት ያሳኳቸው እንደ አድዋ ያሉ ዘመን አይሽሬ ድሎች እንዳሉም አውሰዋል። አሁንም የጋራ ድልን ማስቀጠልና በሁሉም መስክ የተሻለች ሀገር መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
በሀሳብ ልዕልና የሚመራ ሥልጡን ፖለቲካን በማዘመን እና ከልዩነት ይልቅ አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት እንደ ሀገር አብሮነትን ማጽናት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን መጻኢ ጊዜ የተሻለ በሚያደርጉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ መሥራትም ከሁሉም እንደሚጠበቅም አቶ አደም አስገንዝበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አመራር እና አባላትም ኅብረ ብሔራዊ አብሮነትን በማጠናከር ረገድ አርዓያ መኾን እንዳለባቸው አመላክተዋል። አመራሮች ሀገርን ለማሻገር በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ስፖርት ጤናማ ዜጋን ለመፍጠር ቁልፍ መሣሪያ መኾኑን ተናግረዋል። የማኅበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴም ውጤታማ፣ ብቁ እና ንቁ ዜጋን ከመፍጠር አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!