ከ1 ቢሊዮን ብር በጅቶ የመሰረተ ልማት ግንባታ እያካሄደ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ጉጸ።

39

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ አቶ መሐመድአሚን የሱፍ ገለልጸዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ መሰረተ ልማት የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባው ተናግረዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ፣ 15 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የአቅመ ደካሞች ምገባ ማዕከልና መኖሪያ ቤት፣ ድልድይና አረንጓዴ ልማት ይገኙበታል ብለዋል ከንቲባው።

የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በበጀት ዓመቱ ውስጥ ለማጠናቀቅ በተያዘው ዕቅድ መሰረት በጥራት እንዲፈጸም ከወዲሁ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ የጀመረውን ሁለተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልእክት አስተላልፈዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪው አቶ ሁሴን ሰይድ በአካባቢያቸው ለተሸከርካሪ ምቹ መንገድ ባለመኖሩ በመስኖ የሚመረተውን ምርት ለገበያ ለማቅረብ እንደሚቸገሩ አስተያየታቸውን ተናግረዋል። ከመሃል ከተማው እስከ አካባቢያቸው ድረስ የመንገድ ግንባታ ሥራ መጀመሩ የረጅም ጊዜ ችግራቸውን ይፈታል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም የአካባቢቸውን ነዋሪዎች በማስተባበር ለመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል። ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ዚነት መሐመድ በአካባቢያቸው ነባሩ መንገድ በመበላሸቱና መሸጋገሪያ ድልድይ ባለመኖሩ ሲቸገሩ እንደቆዩ ጠቅሰዋል። አሁን እየተሠራ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ምቹ መንገድ ባለመኖሩ በምጥ የተያዙ እናቶችን ወደ ሕክምና ተቋም ለማድረስም ኾነ ገበያ ለመሄድ ችግር እንደነበር አመልክተው የመንገዱ ግንባታ ይሄን ችግር ይፈታል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ባለፈው ዓመትም አንድ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመገናኛ ብዙኀን ችግሮች እንዲፈቱ እየሠሩት ያለው ሥራ የሚመሰገን እንደኾነ ተቋማት ገለጹ፡፡
Next articleበሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የተመራ ልኡክ ጅግጅጋ ገባ።