
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቶትንሃም ሆትስፐር አማካኝ ተጫዋቹ ፓፔ ማታር ሳረር በክለቡ ለስድስት ዓመት ተኩል እንዲቆይ አዲስ የኮንትራት ውል አስፈርሟል።
ተጫዋቹ በ2021 ለቶትንሃም ቢፈርምም በውሰት ውል ለፈረንሳዩ ሜትስ ክለብ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና ቶትንሃም አሁን ከተጫዋቹ ጋር ለስድስት ዓመት ተኩል የሚያቆየውን አዲስ ውል ተፈራርሟል።
አዲሱ ስምምነት እስከ 2030 ክረምት ድረስ በክለቡ እንዲቆይ ያደርገዋል ነው የተባለው። የ21 ዓመቱ ሴኔጋላዊ ተጫዋች በፕሪምየር ሊጉ ለቡድኑ 18 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል።
ሳርር ጥር 13/2024 በሚጀምረው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በሴኔጋል ብሔራው ቡድን በቋሚ ተሰላፊነት ተካቷል፡፡
በሌላ ዜና የማንቸስተር ዩናይትዱ የክንፍ መስመር ተጫዋች ጃዶን ሳንቾ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን በውሰት ውል ሊቀላቀል ይችላል ተብሏል። ተጫዋቹ ስለዝውውሩ ከኤሪክ ቴን ሃግ ጋር እንደተወያየ ነው ቢቢሲ ስፖርት የዘገበው፡፡
የ23 ዓመቱ እንግሊዛዊው የክንፍ ተጫዋች ማንቸስተር ዩናይትድን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2021 የተቀላቀለው በ73ሚሊዮን ፓውንድ ወይም በ85 ሚሊዮን ዩሮ ነበር፡፡ለክለቡም ከ2021 ጀምሮ በ58 ጨዋታዎች ተሰልፎ ዘጠኝ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!