የለማውን ጥጥ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት በሚውል መልኩ በጥራት እየተሰበሰበ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።

23

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በ23 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ጥጥ እየተሰበሰበ መኾኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል። በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጌትነት ካሳሁን እንደተናገሩት በመኽር ወቅቱ የለማውን ጥጥ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት በሚውል መልኩ በጥራት የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በዞኑ በጥጥ ከለማው አጠቃላይ መሬት ውስጥ 12 ሺህ 700 ሄክታሩ በአርሶ አደሮች የለማ ሲኾን ቀሪው ደግሞ በባለሃብቶች የለማ መኾኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ በ7 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ጥጥ መሰብሰቡን ጠቅሰው እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ምርቱን ሙሉ በሙሉ ሰብስቦ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በጥጥ ከለማው መሬትም ከ340 ሺህ ኩንታል በላይ የጥጥ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቡድን መሪው ገልጽዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ከተገነቡ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች እና የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ጥጡ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚደረግ መኾኑንም አቶ ጌትነት አመልክተዋል።

በመኽር ወቅቱ 10 ሄክታር መሬት በጥጥ ማልማታቸውንና ከዚህም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ የገለጹት ደግሞ ባለሀሃብቱ አርሶ አደር ደስታው አወቀ ናቸው። በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ያለውን የጥጥ ምርት በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ እንዲቻል ከጥጥ መዳመጫና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል።

ሌላኛው በመተማ ወረዳ የሽመለጋራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደረጀ አለልኝ ባለፈው የመኽር ወቅት 3 ሄክታር መሬት በጥጥ ሸፍነው ከግማሽ በላይ የሚኾነውን መሰብሰባቸውን ተናግረዋል። ካለሙት መሬት ከ45 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ጠቅሰዋል። እስካሁንም ምርት ካነሱበት መሬት 23 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት የጥጥ ዋጋ ረክሶ እንደነበር አርሶ አደሩ አስታውሰዋል። በዚህ ዓመትም ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም የሚመለከተው አካል ተገቢውን የገበያ ትስስር እንዲፈጥርላቸው ጠይቀዋል። በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ33 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ ለምቶ ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን መምሪያውን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዛሬ ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች መድረክ በሐረር ከተማ ይካሄዳል።
Next articleቶትንሃም ፓፔ ማታር ሳረር ለስድስት ዓመት ተኩል በክለቡ እንዲቆይ አዲስ የኮንትራት ውል አስፈረመ።