“የክልሉ ሕዝብ የተጋረጡበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ሳንቲም ሳትቀር መቆጠብ አለበት፡፡” አቶ መኮንን የለውምወሰን

532

Image result for amhara credit association

የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ባንክ ለመሆን የተጀመረው እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን የሕዝቡ የመቆጠብ አቅም መጎልበት እንዳለበት የአብቁተ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናገሩ፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መኮንን የለውምወሰን በተያዘው ዓመት መጨረሻ አብቁተ ባንክ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ አብቁተ የክልሉ የፋይናንስ ተቋም በመሆን የተቋቋመው  በመደበኛ የባንክ አገልግሎት ሥርዓት ውስጥ ላልታቀፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የብድር እና የቁጠባ አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ የተለያዩ ማኅበራዊ ኃላፊነቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው ተቋሙ የሀዋላ አገልግሎትገንዘብ የማስተዳደር እና የኢንሹራንስ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መኮንን የለውምወሰን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው መረጃ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም እድገትና አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ለክልሉ ሕዝብ የሚሰጠው የብድርና የቁጠባ አገልግሎትም እያደገ ይገኛል፡፡ በተለይም የወጣቶችን ህይወት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀየርም አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት፡፡ በመሆኑም እድሉን ለመጠቀም ወጣቶች ትጉህና ለመለወጥ ቁርጠኛ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

አሁን ካለበት “ማይክሮ ፋይናንስ” ወደ ባንክ ለማሳደግ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ መቅረቡን አቶ መኮንን አስታውቀዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክም በጉዳዩ ላይ እየሠራና ህጉን የማደራጀት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ምላሽ አግኝቶ ባንክ የመሆን ተስፋ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ተቋሙ ጥያቄውን ከማቅረብ ጎን ለጎን ግንባታዎችን እያከናወነ እና በተለያዩ ጉዳዮች እየተጠናከረ ይገኛል፡፡ 

አብቁተ ባንክ ሲሆን ደግሞ የሚሰጠው አገልግሎት እና የኢንቨስትመንት አቅሙ አብሮ ያድጋል፡፡ ኢንቨስትመንት መሠረቱ ቁጠባ ቢሆንም በተለይ ከተቋሙ ጋር በተያያዘ ቀደም ብሎ የነበረው የቁጠባ ባህል ደካማ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የሕዝቡ የቁጠባ ትጋት እና ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋምን ባንክ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን ሕዝቡ በተቋሙ የመቆጠብ ባህሉን ሊያሳድግ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡  በመሆኑም “የክልሉ ሕዝብ የተጋረጡበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ሳንቲም ሳትቀር ወደ ቁጠባ ማምጣት አለበትብለዋል፡፡ ጥሪት መፍጠር፣ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት የተሰናሰሉ መሆናቸውን በመግለጽም የተቋሙን እድገት በማጠናከር ግዙፍ ባንክ የመሆን ህልሙንም እውን ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

 

Previous articleየወደብ ግንባታውን ተከትሎ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
Next articleወልዲያ በሚካሄደው ክልል አቀፍ የስፖርት ውድድር ላይ ዋንጫ ለማንሳት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር አስታወቀ፡፡