“በአዲስ መልክ የሸማች ማኅበራትን በማቋቋም ዘመናዊ እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን በመገንባት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እንሠራለን” ዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ

27

ደሴ: ታኅሳሥ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የከተማ ልማት ክላስተር በሥሩ ከሚያሥተዳድራቸው ተቋማት ጋር የ5 ወራት የሥራ አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡

በግምገማው የተገኙት ቢሮ ኀላፊዎች የኑሮ ውድነቱ ባልተረጋጋ የገበያ ሥርዓት የሚመጣ መኾኑን በመጥቀስ “ሸማች ተኮር የገበያ ሥርዓት በመዘርጋት በተደራጀ አቅም እና ቅንጅት በመሥራት ችግሩን እንፈታለን” ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የአማራ ክልል የተለያዩ የቢሮ ኀላፊዎች እና ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት የገቢ ሥርዓቱን በማዘመን እና በተገቢው መንገድ በመሰብሰብ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ የኢንቨስትመንት፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት፣ የሥራ እና ሥልጠና እንዲኹም የቱሪዝም እና የትራንስፖርት ተቋማት ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፤ አፈጻጸማቸውም ተገምግሟል፡፡

“የአማራ ክልል በተለይ ገቢ በመሰብሰብ ሂደት ውስጥ ክልሉ በፀጥታ ችግር ወስጥ ቢኾንም በችግር ውስጥ ኾነን ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ መሠብሰብ ችለናል” ሲሉ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማህሙድ ገልጸዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በክልሉ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ለመቅረፍ በክልሉ ከ85 በላይ ከተሞች ላይ በአዲስ መልክ የሸማች ማኅበራትን በቅርብ ቀን ውስጥ በማቋቋም ዘመናዊ እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን በመገንባት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እንሠራለን ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማካተት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚሠራ ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ሥምምነት በመፈረሙ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የደስታ መልዕክት አስተላለፈ።
Next articleየሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች ድሬዳዋ ገቡ።