
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተጠናከረ እና በቅንጅት የሚሠራ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም እንደሚጀመር ተገልጿል። ከተማ አሥተዳደሩ ለ25 ሺህ ተማሪዎች በቅርቡ ምገባ ለማስጀመር በሚያስችል እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በኃይሉ ገብረሕይወት የፕሮግራሙን መነሻ እቅድ አቅርበዋል። ምገባው በ47 ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚኾን ነው የገለጹት። በአጠቃላይ ለ25 ሺህ ተማሪዎች ተደራሽ ይኾናል፤ በ10 ወራት ውስጥ 117 ሚሊዮን 820 ሺህ ብር ወጭ እንደሚያስፈልግም አቶ በኀይሉ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም ከመንግሥት በተጨማሪ ፋብሪካዎችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ፣ ረጅ ድርጅቶችን፣ ነጋዴዎች እንዲሁም መላውን ማኅበረሰብ በማሣተፍ የበጀት ምንጭ ተደርጎ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የተማሪ ምገባ ፕሮግራምን በትምህርት ቤቶች ማስጀመር አላማው ብቁ ዜጋን የማፍራትና ትውልድ የመቅረጽ ነው ብለዋል። ካለን ላይ ቀንሰን የነገ ሀገር ተረካቢዎችን የምንደግፍበት መልካም እሳቤ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የምገባውን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ከከተማው ውጭ ያሉ የሃብት አማራጮችን አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል። የበጀት ምንጮቻችን ባላቸው አቅም ልክ እንዲያዋጡ ማድረግና በተማው የዳቦ ፋብሪካ እንዲገነባ ይሠራልም ሲሉ ብለዋል።
የተማሪ ምገባው ፕሮግራሙን ለሕዝብ ማሣወቅና ተግባሩን በጥብቅ አሠራር እና ክትትል እንደሚደረግ እና በቅርብ ጊዜ እንደሚጀመር ጠቁመዋል። ትምህርት ቤቶችንና ተቋማትን የማስተሳሰር ሥራ መሠራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!