
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ወደብን ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈጸሟን ይፋ ካደረገች በኋላ የዓለም መገናኛ ብዙኅን ጉዳዮን እየተቀባበሉት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባሕር በር እና የወደብ ፍላጎቷን ለሚዲያዎች ግልጽ በኾነ መንገድ ካወጣች ከወራት በኋላ ወደብ የምታገኝበትን ስምምነት ፈጽማለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ታሪካዊ የተባለለትን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ የብዙዎች መነጋገሪያ ርእሰ ጉዳይ ኾኗል፡፡ የታላቋ ብሪታኒያ ሚዲያ ቢቢሲ የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ ወደብ እንድትጠቀም የመጀመሪያውን ሕጋዊ እርምጃ ወስዳለች በሚል መንግሥት አስታውቋል ሲል ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያ የተፈራረመችው ስምምነት የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ አንዱ የኾነውን ወደብ እንድትጠቀም ነውም ብሏል፡፡ ቢቢሲ በዘገባው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቀይ ባሕር ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ማንሳታቸውን አስታውሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወርኃ ጥቅምት የሰጡት የባሕር በር ጥያቄ በምሥራቅ አፍሪካ ውጥረት ፈጥሮ ቆይቷልም ይላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት የባሕር በር ጥያቄ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሊጋጭ እንደሚችል ስጋት ውስጥ ከትቶ እንደነበርም ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡
የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ለማረጋገጥ መንገድ እንደሚከፍት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውንም ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ በርበር ወደብ የጦር ሠፈር እንደሚኖራትም ዘገባው አትቷል፡፡
የኳታሩ አልጀዚራ ደግሞ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ወደብን ለመጠቀም ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራረመች ሲል ዜና አውጥቷል፡፡ የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ የበርበርን ወደብ ለመጠቀም ስምምነት መፈረሟን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ የባሕር ላይ ንግድ በአብዛኛው በጎረቤቷ ጅቡቲ በኩል መኾኑንም በዘገባው አንስቷል፡፡ ኤርትራ ራሷን የቻለች ሀገር ከኾነች ጀምሮ ኢትዮጵያ ባሕር አልባ ሀገር ኾና መቆየቷንም በዘገባው አስታውሷል፡፡
አልጀዚራ በዘገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከሶማሊላንድ ወንድሞቻችን ጋር ተስማምተን ተፈራርመናል” ማለታቸውንም ዘግቧል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስምምነቱን ታሪካዊ ሲል ገልጾታልም ብሏል አልጀዚራ፡፡ ስምምነቱ ኢትዮጵያ የባሕር በርን አስተማማኝ ለማድረግ እና ወደብ የማግኘት እድልን ለማስፋት ያላትን ፍላጎት እውን ለማድረግ የሚያስችል መንገድ ነው ሲል ዘግቧል፡፡
ሮይተርስ በበኩሉ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ ስምምነት የጦር ሰፈር እንድታገኝ እና የባሕር ላይ ንግድ እንድታካሂድ በር እንደሚከፍት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መግለጻቸውን ዘግቧል፡፡ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚኖራት አማካሪው ገልጸዋልም ብሏል፡፡
ሌላኛው ፍራንስ 24 ኢትዮጵያ የባሕር ወደብ ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ታሪካዊ ስምምነት ተፈራራመች ሲል ዘግቧል፡፡ የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወደቦችን ትፈልጋለች ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ያደረገችው ስምምነት በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ የኾነችው ሀገራቸው የባሕር በር የመጠቀም መብቷን እንደምታረጋግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተናገሩ ከወራት በኋላ ነው ሲል ያትታል፡፡
የበርበር ወደብ ለኤደን ባሕረ ሰላጤ እና ለስዊዝ ካናል ሁነኛ ቦታ መኾኑንም አንስቷል፡፡ የተደረገው ስምምነት የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና የጸጥታ አጋርነታቸውን እንደሚያጠናክርም ሮይተርስ በዘገባው አመላክቷል፡፡
የስምምነቱን ጉዳይ የዘገበው ፒቢስ ኒውስ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር ወይም 12 ነጥብ 4 ማይል ቦታ በባሕር ዳርቻዋ ለመስጠት መስማማቷን ዘግቧል፡፡ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በዓለም ብዙ ቁጥር ሕዝብ ያላት ወደብ የሌላት ሀገር እንደነበረችም አንስቷል፡፡ ስምምነቱ ለሚመጣውም ኾነ አሁን ላለው ትውልድ አንድ እርምጃ የቀደመ መኾኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን መግለጻቸውንም ጽፏል፡፡
የአሜሪካ ድምጽ ስምምነቱን በተመለከተ ባወጣው ዘገባ የመግባቢያ ሰነዱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ላለው ዘርፍ ብዙ አጋርነት ማዕቀፍ ኾኖ ለማገለግል የታሰበ ነው ተብሏል ሲል ዘግቧል፡፡ የመግባቢያ ሰነዱ የደኅንነት፣ የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ አጋርነታቸውንም እንደሚጠናከር የታመነበት መኾኑንም አንስቷል፡፡
ቲአርቲ አፍሪካም በዘገባው የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በርበር ወደብን ለመጠቀም የመጀመሪያ ስምምነት ተፈራረመች ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ በተፈራረመችው የወደብ ስምምነት የጦር ሰፈር እንደምትገነባም አንስቷል፡፡
በታሪክ በርካታ ወደቦች የነበሯት እና በቀይ ባሕርም የማዘዝ ሥልጣን የነበራት ኢትዮጵያ በዓለም የፖለቲካ መቀያየር እና በሌሎች ውጫዊና ውስጣዊ ጉዳዮች የባሕር በር ካጣች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለወትሮው ባለ ብዙ ወደቦች የነበረችው እና በቀይ ባሕር ከፍ ያለ ስምና ዝና የነበራት ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ክብሯ ትመለስ ዘንድ ጥያቄ ማንሳት ከጀመረች ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥሯ እና ከታሪካዊ ተጠቃሚነቷ ጋር የሚስማማ የባሕር በር ሕጋዊ በኾነ መንገድ ላገኝ ይገባኛል በማለት ለውይይት በሯን ከፍታለች፡፡ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከውስጥ ለውስጥ አልፎ በአደባባይ ሲወጣ በርካቶችን ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያም ጥያቄዋን በአደባባይ ከጠየቀች ከወራት በኋላ ለቀይ ባሕር ተጠቃሚነት መግቢያ በር ነው የተባለለትን ሁነኛ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ ይሄም ስምምነት በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ ታሪካዊ ተብሏል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!