የተገኘው የባሕር በር የኢትጵያን ስብራት የጠገነና የትውልድን የዘመን ቁጭት የመለሰ መሆኑ ተገለጸ።

68

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተገኘው የባሕር በር የኢትጵያን ስብራት የጠገነና የትውልድን የዘመን ቁጭት የመለሰ መሆኑ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትቴር ገለጸ፡፡

የተገኘው የባሕር በር የወጪና ገቢ እቃን ከማመላለስ ባለፈ ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገትና ሉዓላዊነት መረጋገጥ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል የሚለውን ጉዳይ በተለያዩ መድረኮች ሲያነሱ ያላመኑ፤ ከንቱ ቅዠት የመሰላቸውና ይልቁንም ሀገራችንን ወደ ጦርነት ሊወስዷት እንደሆነ ስጋት ያደረባቸው ብዙዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድና በጋራ የመልማት መርህን በመከተል በተግባር ማየት ችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የባሕር በር ማግኘት አንዱ የኢትዮጵያ ምንዳ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የእኛ የባሕር በር ማግኘት የሚጎዳው አካል የለም፤ የእኛ ፍላጎት በጋራ ማደግ፣ በጋራ መበልፀግ፣ በጋራ ደኅንነትን ማስጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

አሁን የተገኘው የወደብ አማራጭ በአሁኑ ሰአት በምንጠቀማቸው ወደቦች ላይ ለውጥ ሳናደርግ የሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በሚፈልገው ልክ አስፍተን የምንጠቀምበት ስለሆነ ሌሎችን የሚያሰጋ አንዳችም ነገር እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባደረጉት ብርቱ ጥረት ለሀገራችን ያስገኙትን ወደብ ለሎጂስቲክስ ዘርፋችን እና ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት በታሰበው ልክ ለመጠቀም የሴክተሩ ሠራተኞች ዝግጁነታችንን ማረጋገጥ ይገባል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላማዊ ውይይቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመጡ መቃኘት፤ በዘላቂነትም መተግበር ይገባቸዋል” የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር
Next articleየኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት እና የዓለም መገናኛ ብዙኅን ዕይታዎች