“ሰላማዊ ውይይቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመጡ መቃኘት፤ በዘላቂነትም መተግበር ይገባቸዋል” የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር

50

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አለመግባባት ወደ አፈሙዝ እየዞረ ከፖለቲካ ምክሩ እና ዝክሩ ያልነበሩ ንጹሐን ተቀጥፈዋል፡፡ ለዓመታት የተገነቡ ተቋማት ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል፡፡ ነገ ሀገራቸውን የሚረከቡ ሕጻናት እና ወጣቶች ፖለቲካ በወለደው ግጭት አልፈዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የፖለቲካ አለመግባባት በፈጠረው ጦርነት ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ብዙዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ጥሪታቸውንም አጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር በትርሊዮን የሚቆጠር ሃብቷን አጥታለች።

ሰላማዊ ውይይቶች ከጦርነት እየዘገዩ፣ ጦርነቶች ደግሞ ከሰላማዊ ውይይቶች እየፈጠኑ ሀገር በማያባራ ግጭት እና ጦርነት ውስጥ እንድትጓዝ ተገድዳለች፡፡ በአንድ በኩል ያለው ግጭት የተፈታ ሲመስል ሌላ እየተፈጠረ ኢትዮጵያ ያጣችው ብዙ ነው፡፡

ሰላማዊ ውይይት አያስፈልገንም ተብሎ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሰላም እናቶች ምክር እና ተማጽኖ ወደ ጎን በመተው የተጀመረው ጦርነት ቁጥር ስፍር የሌለው ጉዳት እና ኪሳራ አድርሶ የመጀመሪያው መጨረሻ ላይ መጥቶ በሰላማዊ ውይይት ሲቋጭ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ምንም እንኳ የፖለቲካ ጡዘት በወለደው ጦርነት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተጎጂዎች ቢኾኑም የአማራ ክልል ደግሞ ግንባር ቀደም ተጎጂ ኾኖ ቆይቷል፡፡ አሁንም በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት እና ግጭት ክልሉን ከእርምጃው እየጎተተው ነው፤ የሰው ሕይወት ማጣትን ጨምሮ በርካታ ሀብትና ንብረት አሳጥቶታል፡፡

በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት እና ክልሉን ለማረጋጋት የሰላም ጥሪ ቀርቧል፡፡ የሰላም ጥሪውም ተስፋ ሰጪ ምላሾችን አሳይቷል፡፡ ክልሉም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ መኾኑን የክልሉ መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ከሰሞኑም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በአማራ ክልል በተደረገው የሰላም ጥሪ በርካቶች ሰላምን መምረጣቸውን አንስተዋል፡፡ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ አንጻራዊ ሰላም ተፍጠሯልም ብለዋል፡፡ በክልሉ ከማረጋጋት ሰላምን ወደ ማጽናት መሸጋገር መቻሉንም አንስተዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግሥት የሰላም በሮችን ለሁሉም ክፍት አድርጓል፤ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት እና አቋም መቼም ቢኾን አይቀየርም፡፡

በእያንዳንዱ የሰላም ቀን እያንዳንዱ ዜጋ ተጠቃሚ እንደኾነ መንግሥት እምነት አለውም ብለዋል፡፡ የሕዝብ ፍላጎት እንዲሳካ ሁሉም አካላት ሰላምን ለማጽናት፣ ሀገርን ከውድመት ለመታደግ ቀናኢ እና ተባባሪ መኾን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በአማራ ክልል በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን መንግሥት ለይቶ እንደሚያውቃቸው፣ የሚፈቱበትን አቅጣጫም ማስቀመጡን እና ለመፍታት ርብርብ ማድረግ መጀመሩንም አንስተዋል፡፡ በሌሎች ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ የሌሎችን ሕመም እና ስሜት መረዳት፣ የራስን የዜግነት ድርሻ እና ግዴታ መወጣት፣ ከችግር ፈጣሪነት ይልቅ የመፍትሔ አካል መኾን እና ለዘላቂ ሰላም መተባበር ያስፈልጋል ነበር ያሉት፡፡ ከሰላም ውጭ ያሉት አማራጮች ሀገርን እንደሚጎዱም አንስተዋል፡፡

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ማብሬ ታዴ የትኛውንም ኃይል እና ጉልበት ቢኖር የግጭት የመጨረሻው መቋጫ እና መፍቻ ሰላምና ድርድር ነው ይላሉ፡፡ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መቋጨት ደግሞ አብዛኛው የሚስማማባት ነው፤ ሰላማዊ ውይይትን ከግጭት በኋላ ሳይኾን ከግጭት በፊት መጠቀም፣ ወደ ግጭት የሚያስገቡ ጉዳዮችን አስቀድሞ በውይይት መፍታት ከመገዳደል ያድናል ነው የሚሉት፡፡

ግጭቱ ከመነሳቱ አስቀድሞ ውይይት ቢደረግ ኖሮ የሰው ሕይወትን እና የንብረት ውድመትን መታደግ ይቻል እንደነበርም ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ “ፈጽሞ ከመቅረት መዘግየት ይሻላል” በሚለው ብሂል አሁንም ቢኾን ውይይት ማድረግ አትራፊ እንጂ አክሳሪ አይደለም ይላሉ፡፡ እንደ መምህሩ ገለጻ ውይይት የማንኛውም ጉዳይ ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ በክልሉ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ፖለቲካውን ይጠግናል፤ ምጣኔ ሃብቱን ከውድቀት ይታደጋል፤ ማኅበራዊ ሕይወትንም ያስተካክላል ነው የሚሉት፡፡

ሰላማዊ ውይይቱ የበለጠ ጥሩ እና መልካም የሚኾነው ችግሮችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲፈታ ኾኖ ሲደረግ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሰላማዊ ውይይትን ለአንድ ሰሞን ብቻ መጠቀም ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ይኾናልም ይላሉ፡፡ ሰላማዊ ውይይቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመጡ መቃኘት፣ በዘላቂነትም መተግበር ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ እንደ መምህሩ ገለጻ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ሁሉም ኃይሎች ለሰላም መጠራት አለባቸው፤ ከየትኛውም አካል ይነሳ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በግልጽ ማሳወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ጥያቄዎችን ለመፍታት ሁሉንም ማሳተፍ መተማመን እንዲፈጠር ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡ የሂደቱ አሳታፊ መኾን ዘላቂ ሰላምን ያመጣል፤ ተዓማኒነትንም ያዳብራል ነው የሚሉት፡፡ በረጅም፣ በመካከለኛ እና በአጭር ጊዜ የሚፈቱ የሕዝብ ጥያቄዎችን በምክክር እና በሕግ ጉዳይ መፍታት ይገባልም ብለዋል፡፡ የጥያቄዎች ሂደት ማወቅ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ያደርጋልም ባይ ናቸው፡፡

ችግሮችን በግጭት ከመፍታት ባሕል በመውጣት በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባሕልን ማዳበር ይገባል የሚሉት መምህሩ ሰላማዊ አካሄዶችን አለመንፈግ ተገቢ ነውም ይላሉ፡፡ ለግጭት መነሻ የሚኾኑ ችግሮችን ትኩረት አለመስጠት እና ወደ ግጭት ከማደጋቸው አስቀድሞ በውይይት አለመፍታት ዋጋ እንደሚያስከፍልም አንስተዋል፡፡ ሰላም አያከስርም፣ ነገር ግን ጊዜ ያስፈልገፈዋል፤ ዋጋም ያስከፍላል፤ ምንም ቢኾን ወደ ግጭት አንሄድም የሚል ሀሳብ መጎልበት አለበትም ይላሉ፡፡

እንደ መምህሩ ገለጻ ሰላማዊ አማራጮችን ከመመልከት ይልቅ ሁሉንም በጥርጣሬ መመልከት፣ ወደ ሴራ ትንታኔ መውሰድ የተለመደ ተግባር ኾኗል፤ የሴራ አካሄድ ደግሞ ሁሉንም እየጎዳ ነው፡፡ ሥርዓት የሚጸናው በሂደት ነው የሚሉት መምህሩ ሰላማዊ ልምምድን በማጎልበት ሰላማዊ አካሄድ ማጽናት ይገባል ይላሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በነበረው ግጭት እና ጦርነት በግለሰብ እና በማኅበረሰብ ደረጃ ያልከሰረ የለም፤ ከኪሳራ ለመውጣት ከኃይል እርምጃ መውጣት፤ ዲሞክራሲን መለማመድ፣ ችግሮችን ቁጭ ብሎ በመወያዬት መፍታት የተገባ ነው ብለዋል መምህሩ።

ከጥርጣሬ ነጻ የኾኑ ተቋማትን መገንባት፤ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር መርሕ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር ይገባልም ብለዋል፡፡ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሕዝብ ጥያቄዎችን በመፍታት ፋይሉን መዝጋት ይገባልም ይላሉ፡፡ ያደሩ ጉዳዮችን መፍትሔ መስጠት፣ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን በቂ ዝግጅት በማድረግ መፍታት ከተቻለ ክልሉ አሁን ካለበት ኹኔታ ይወጣልም ነው ያሉት፡፡

እኔ ነኝ ጉዳዩን የማውቀው፣ ከእኔ በላይ ችግሩን የሚተነትነው፣ መፍትሔውንም የሚቀምረው የለም የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ የችግሩ ሰለባዎች አለመኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የሃይማኖት አባቶችንም ለምን ምክር እና ተግሳጽ ሰጣችሁ በሚል ድፍረት የተመላበት አነጋገር እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል፡፡ ይህ ዓይነት አካሄድ ሕዝብን ይጠቅማል የሚል እምነት እንደሌላቸውም አንስተዋል፡፡

ስለ መብት መከራከር፣ ሰዎች ጥቃት ሲደርስባቸው ለምን ብሎ መጠየቅ እና ለመፍትሔው መወትወት፣ ለተገፉት መቆም ጥሩ እና የሚደገፍ ነው የሚሉት መምህሩ ሁሉንም በጥርጣሬ ማዬት ግን ልክ አይደለም ነው ያሉት፡፡

የሰላም ውይይቶችን በጥርጣሬ የሚመለከቱ አብዛኛዎቹ የችግሩ ገፈት ቀማሾች ላይኾኑ እንደሚችሉም አንስተዋል፡፡ የሰላም ውይይቱን በጥርጣሬ መመልከት እና በጥርጣሬ እንዲታይ የሚያደርጉ ሁሉ የእኛ ሃሳብስ እንዲህ ቢኾን እንወዳለን? ብሎ መጠየቅ ይገባቸዋልም ይላሉ፡፡ በሰላም የሚያገኙት ትርፍ በግጭት ከሚያገኙት ትርፍ የቀነሰ ከኾነ ሰላማዊ አማራጮች ጥቅም ላይ እንዳይወሉ እንደሚገፋፉም ያመላክታሉ፡፡

ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ እስከ መጨረሻው ድረስ ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም የተሻለው እና አዋጩ ነውም ይላሉ፡፡ ዝምተኛው ብዙኃን የሚባለው ሕዝብ አለመናገሩ እውነታው እንዳይገለጥ፣ እውነት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚመላሰለው ብቻ እንዲመስል አድርጎታል ነው የሚሉት፡፡ የሕዝብን እውነት መረዳት እና ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም ዘላቂ ሰላምን ያመጣልም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቡና ባንክ መምህራንና የጤና ባለሙያዎችን ለመደገፍ ባዘጋጀው የ3ተኛ ዙር ይቆጥቡ ይሸለሙ መርሐ ግብር ለእድለኞች ሽልማታቸውን አስረከበ፡፡
Next articleየተገኘው የባሕር በር የኢትጵያን ስብራት የጠገነና የትውልድን የዘመን ቁጭት የመለሰ መሆኑ ተገለጸ።