
አዲስ አበባ: ታኅሳሥ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቡና ባንክ መምህራንና የጤና ባለሙያዎችን ለመደገፍ ያዘጋጀውን የ3ተኛ ዙር ይቆጥቡ ይሸለሙ መርሐ ግብር ማጠናቂያ ፕሮግራምን አካሂዷል። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የቡና ባንክ ማርኬቲንግ እና ኮምዩኒኬሽን ዳሬክቶሬት ተወካይ ካሳሁን ይበልጣል ቁጠባ የእድገት መሰረት ነው ብለዋል፡፡
መቆጠብ ሃብትን ማከማቸት ላይ ያተኮረ ተግባር ብቻ ሳይኾን ብሩህ የኾነ የወደፊት ህልሞችን እውን ለማድረግና አቅምን ለማሳደግም የሚረዳ ጠቃሚ መንገድ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ የሽልማት መርሐ ግብሩ ባለሙያዎች ለሀገር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ያለውን አድናቆት የሚገልጽበት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የቁጠባ ባሕልን በማሳደግ የፋይናንስ ደኅንነትን በአስተማማኝ እንዲረጋገጥ ባንኩ የሚያደርገውን ጥረት በተግባር የሚያሳይበት እንደኾነም አቶ ካሳሁን አብራርተዋል።
ባንኩ በዋናው መስሪያ ቤት ባካሄደው የሽልማት አሰጣጥም ለባለድለኞች የአውቶሞቢል፣ የላፕቶብ፣ የታብሌት እና የስልክ ሽልማቶችን አበርክቷል። የወልድያ ቅርንጫፍ ደንበኛ መምህር ፈንታየ ደምሌ አሸናፊ የኾኑበትን የቤት አውቶሞቢል ሽልማት ተቀብለዋል።
ዘጋቢ:- ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!