ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ታሪካዊ የኾነ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

34

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ታሪካዊ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ ፈርመዋል።

የኢፌድሪ መንግስት እና የሶማሌላንድ መንግስት የፈረሙት የትብብር እና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ በተለያዩ ዘርፎች በቀጣይ ለሚኖር ግንኙነታቸው ማዕቀፍ የሚሆን ነው። ይህ የመግባቢያ ሰነድ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እውን የሚያደርግ፣ የባህር በር አማራጮችን የሚያሰፋ፣ የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናከር መኾኑ ተገልጿል።

ሰነዱ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲ ዘርፍ የሚኖራቸው ግንኙነት የሚጎለብትበትን አካሄድ የሚያካትት ነው ተብሏል። ይህ የመግባቢያ ሰነድ የኢትዮጵያ መንግስት በሰጥቶ መቀበል መርህ እና ለጋራ ጥቅም ከጎረቤቶቿ ጋር የመስራት ፍላጎት እና አቋሟን መልሶ የሚያፀና መኾኑ ተገልጿል። ይህ ሰነድ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት እና ለአፍሪካ ቀንድ ትሥሥር የላቀ ፋይዳ ያለው ነው። እንዲሁም ሰነዱ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እና ደህንነት የሚገባትን ሚና እንድትጫወት የተሻለ እድል የሚፈጥር መኾኑን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰበር ዜና!
Next article“ከሶማሌ ላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ለዘመናት ኢትዮጵያ ላይ የተቆለፈውን በር የከፈተ ነው” የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት