ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች እና የጎንደር ሰላምና ልማት ማኅበር በድርቅ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረጉ፡፡

48

ጎንደር: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች እና የጎንደር ሰላምና ልማት ማኅበር በሰሜን ጎንደር ዞን በድርቅ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ አድርገዋል።

ሁለቱ ማኅበራት ከተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሠበሠቡትን ድጋፍ በጎንደር ከተማ ተገኝተው ለሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር ተወካይ አስረክበዋል።

የግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች የኢትዮጵያ ተወካይ ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ በውጭ የሚገኘው ግሎባል አሊያንስ ከተለያዩ ድርጅቶች የሠበሠበውን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ከ605 ኩንታል በላይ በቆሎ እና ከ12 ሺህ ፓኬት በላይ አልሚ ምግቦችን ከጎንደር ሰላም እና ልማት ማኅበር ጋር በመተባበር በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ማቅረቡን ገልጸዋል።

ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች በቀጣይም ለወገኖቹ ለመድረስ ይሠራል ያሉት ጋዜጠኛ በፍቃዱ በውጭ የሚገኙ የድጋፉ አሠባሣቢዎች ከሕዝቡ ጎን መኾናቸውን መልዕክት አስተላልፈዋል ብለዋል።

የጎንደር ሰላምና ልማት ማኅበርን ወክለው የተገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሀገር ልማት እና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ጌትነት አለሙ (ዶ.ር) በሰሜን ጎንደር ዞን በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ያሠባሠበውን ድጋፍ አስረክቧል ብለዋል። የጎንደር ሰላም እና ልማት ማኅበር በቀጣይም ማኅበረሰቡን ለማገዝ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ዶክተር ጌትነት አብራርተዋል።

በርክክቡ ላይ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሣ በዞኑ የተከሰተው ድርቅ ከ452 ሺህ በላይ ዜጎች የደራሽ ምግብ ድጋፍ እንዲፈልጉ አድርጓል ብለዋል።
የተለያዩ ድርጅቶች እና መንግሥትም ጥናቶችን ያደረጉ ቢኾንም በተጠናው ልክ ድጋፍ እየተደረገ አለመኾኑን ጠቁመዋል።

አቶ ቢምረው ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያ መብቶች እና የጎንደር ሰላምና ልማት ማኅበር ያደረጉት ድጋፍ ዕለታዊ እፎይታን የሚሰጥ ነው ብለዋል። በቀጣይ ሌሎች ተቋማትም ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል::

ዘጋቢ፡- ደስታ ካሣ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“2023 የክርስቲያኖ ሮናልዶ ዳግም የከፍታ ጊዜ”
Next articleሰበር ዜና!