“2023 የክርስቲያኖ ሮናልዶ ዳግም የከፍታ ጊዜ”

56

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ2023 እ.ኤ.አ ዓመት 54 ግቦችን አስቆጥሯል።ይህ የግብ ቁጥር ተጫዋቹን የዓለማችን የዓመቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ኾኖ እንዲያጠናቅቅ አድርጎታል።

ከሳኡዲው አልናስር ጋር አስደናቂ ጊዜን እያሳለፈ ያለው ሮናልዶ በ2022 16 ግቦችን ብቻ ማስቆጠሩን በማውሳት የ2023 ዓመት ለእግር ኳስ ኮከቡ የተለየ እንደነበር ጅኦ ኒውስ አስነብቧል።

በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት ከአሠልጣኝ ቴን ሃግ ጋር አለመግባባት መፍጠሩና ወደ ሳኡዲ አረቢያ ማቅናቱ የሮናልዶ የእግር ኳስ ሕይወት እንደመሸበት ማሳያ ተደርጎ ነበር።

ህልሜ ብዙ ነው የሚለው ሮናልዶ ግን 2023 ከገባ ጀምሮ ለአል ናስር 44፣ ለፖርቱጋል 10 በድምሩ 54 ግቦችን በማስቆጠር ታሪክ ሠርቷል።

ሮናልዶ የዓመቱን 54ኛ ግብ ካስቆጠረ በኃላ “የክለብ አጋሮቸን አመሠግናለሁ” ብሏል በኢንስታግራም ገጹ።

በተደጋጋሚ ጫማ ስለመስቀል እጠየቃለሁ ያለው ተጫዋቹ “በትንሹ ከአል ናስር ጋር አምስት ዋንጫዎችን ማንሳት እፈልጋለሁ” ሲል ህልሙ ረዥም መኾኑን ገልጿል።

ሮናልዶን በመከተል ሃሪኬንና ኪሊያን ምባፔ እያንዳንዳቸው 52 ግቦችን በማስቆጠር ዓመቱን አጠናቅቀዋል።

ኧርሊንግ ሃላንድ 50 ጊዜ ኳስና መረብን ያገናኘ ሲኾን የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል መሲ በዓመቱ 28 ግቦችን ነው ያስቆጠረው።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኑሮ ውድነቱን ችግር ለመቅረፍ ሰላምን በማስፈን ሸማች ተኮር ምርትን ማሳደግ እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን መገንባት ያስፈልጋል” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next articleግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች እና የጎንደር ሰላምና ልማት ማኅበር በድርቅ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረጉ፡፡