
ጎንደር: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ “በተደራጀ አቅም የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት” በሚል መሪ መልዕክት ከጎንደር ቀጣና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ለኑሮ ውድነት መባባስ ዘላቂ ሰላም አለመኖር፣ የምርት ሥርዓቱ አለመዘመን፣ የግብይት ሥርዓት አለመጠናከር እና የሕገ ወጥ ነጋዴ መንሰራፋት ምክንያት መኾኑን አንስተዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ሸማች ተኮር ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ዘመናዊ እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን መገንባት እና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሥራ ኀላፊዎች የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱ በመኾኑ የተሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) በበኩላቸዉ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት አምራቾችን ከሸማቾች ጋር የሚያገናኝ የንግድ ሰንሰለት መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
ክልሉ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የሚያስችላቸው ተጨባጭ ድጋፍ ማድረግ፣ ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል እና የእሑድ ገበያን ማስፋፋት ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ዶክተር ኢብራሂም አንስተዋል።
የግብይት ማዕከላትን ማቋቋም እና ማሻሻል ላይም ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የንግድ እና ገበያ ልማት የሥራ ኀላፊዎች ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ በውይይቱ አንስተዋል።
ዘጋቢ፡- አዲስ ዓለማየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!