
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በየጊዜው በሚነሱ ቫይረሶች ተጋላጭ ከኾኑ የሰውነት ክፍሎች የመተንፈሻ አካላት አንዱ ነው። ቫይረሶች በተደጋጋሚ ወይንም ጊዜ ጠብቀው ሊነሱ ይችላሉ። የሚያሳዩት ምልክት እና ሕመምም እንደዝርያቸው እንደሚለይ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ደዌ፣ የሳንባ እና ጽኑ ሕሙማን ሐኪም ዶክተር ደረጀ ደስታ ነግረውናል።
ዶክተር ደረጀ እንዳሉት የላይኛውን የአየር ቧንቧ ከሚያጠቁ ቫይረሶች ውስጥ ኮሮና እና ኢንፍሎዊንዛ ይገኙበታል። የኮሮና ቫይረስ ከዚህ በፊትም ተከስቶ እንደነበር ያነሱት ዶክተር ደረጀ ከጊዜ ቆይታ በኋላ ዝርያውን በመለወጥ በዓለም ላይ ተከስቶ የሰው ሕይወት ቀጥፏል።
ከሰሞኑም “የኢንፍሎዌንዛ ቫይረስ” መከሰቱን ገልጸዋል። በጉንፋን መሰል ሕመም ከተያዙ ሰዎች የተወሰዱ ናሙናዎች 3 በመቶ የኮሮና፣ እስከ 20 በመቶ የሚደርሱት ደግሞ የኢንፍሎዌንዛ ቫይረስ እንደተገኘባቸው ገልጸዋል።
ሕመሙ የቫይራል ኢንፌክሽን ወይንም ደግሞ የአየር ቧንቧን ሲጠቃ የሚከሰት እንደኾነም ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባለፈ በላይኛው የአየር ቧንቧ የሚገኙትን የሰውነት ክፍሎች በመቀየር ለባክቴሪያ ኢንፌክሽን ቦታ ያመቻቻል። ይህም ለሳንባ ምች በማጋለጥ ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል። ሙቀት እና ቅዝቃዜ ደግሞ የሕመሙ አባባሽ ተደርገው ተቀምጠዋል። ቫይረሱ በተለያየ ጊዜ ሊነሳ የሚችል ቢኾንም በተለይም ደግሞ ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ በአቧራ፣ በአበባ ብናኝ ይበልጥ ሊስፋፋ ይችላል።
በአየር እና ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር በሚደረግ መጨባበጥ አልያም ንኪኪ ይተላለፋል። ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸውን እና የሚያጨሱ ሰዎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።
ማስነጠስ፣ ሙቀት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማንቀጥቀጥ፣ ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ራስ ምታት፣ አፍንጫ ወይንም ግንባር አካባቢ ከፍተኛ የኾነ ሕመም፣ ድካም፣ የጡንቻ መዛል፣ መቆረጣጠም፣ የጀርባ ሕመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የተያዘውን ሰው የሚረብሽ ደረቅ ሳል ምልክቶች ናቸው። ሳሉ ከሕክምና በኋላም እስከ አንድ ወር ሊቆይ ይችላል።
አንድ ሰው ጉንፋን መሰል ሕመም ሲሰማው በቤት ውስጥ በባሕላዊ መንገድ መከላከል እንደሚገባ እንደ መፍትሔ አስቀምጠዋል።
እረፍት በማድረግ፣ የመከላከያ አቅምን የሚገነቡ እንደ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ቫይታሚን ሲ እና ኢ ያላቸው ምግቦች መመገብ፣ ትኩስ ነገሮችን እና ማስታገሻ በመውሰድ መከላከል ይገባል ብለዋል ዶክተር ደረጀ።
የቫይረስ ኢንፌክሽን በሚከሰትበት ወቅትም የሙቀት እና ራስ ምታት መድኃኒት መውሰድ ሌላኛው አማራጭ ነው። የቫይረስ ኢንፌክሽንን ተከትሎ የሚመጣ እንደ ሳንባ ምች የመሳሰሉ ሕመሞች በሚያጋጥም ጊዜ ደግሞ ሕክምና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ የቅድመ መከላከል ሥራ ላይ ማተኮር እንደሚገባም መክረዋል። ከሦስት እስከ አምስት ቀን ለአንድ ሰዓት ያህል እንቅስቃሴ ማድረግ የሳንባን አቅም እና የመከላከል ችሎታውን ይጨምራል። በቀላሉ ከኢንፌክሽን ተጋላጭነት ይከላከላል።
ክብደት መቀነስ፣ ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ሰዎች መድኃኒቱን በተገቢው መንገድ መውሰድ፣ ከሱስ ራስን ማቀብ፣ ከጭስ ራስን መጠበቅ፣ የግል እና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ዋነኛዎቹ ጉዳዮች ናቸው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!