ዶክተር አሚር አማን በሥጦታ ያገኙትን 1 ሚሊዮን ብር ለሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አበረከቱ፡፡

349

ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) የቀድሞው የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶክተር) ከኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ 1 ሚሊዮን ብር ተበርክቶላቸዋል፡፡

ለዶክተር አሚር ዕውቅናው የተሰጣቸው መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅርበትና በትብብር እንዲሠራና በዘርፉ መሻሻሎች እንዲመዘገቡ ላደረጉት አስተዋጽኦ እንደሆነ በምስጋናና ዕውቅና መርሀ ግብሩ ላይ ተገልጧል፡፡

ለኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ያደረጉት የ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍም ሌሎች ባለሀብቶች እና ድርጅቶች ከሥራ ፈላጊዎች ጎን እንዲቆሙ ለማበረታታት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ ብዙዎቹ ዘርፉን ከደገፉ ደግሞ የመነሻ መሥሪያ ገንዘብ የሌላቸው ብዙ የጤና ሙያ ተመራቂዎች ሥራ እንዲፈጥሩና ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ ያግዛል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት አሚር አማን (ዶክተር) የዕውቅና ሽልማቱ ለአንድ ሰው ሳይሆን በግሉ ዘርፍና በጤና ሚኒስቴር በኩል ለተጀመረው መልካም ግንኙነት የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ባለበት የበጀት ውስንነት የተነሳ ሳይቀጥራቸው የሚቀሩ ባለሙያዎችን በመቅጠር የግሉ ዘርፍ እየፈጠረ ላለው የሥራ ዕድልም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እስከ 2012 በጀት ዓመት ማገባደጃ ለ 3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱ ይታወሳል፡፡

ፎቶ፡- ከጤና ሚኒስቴር

Previous articleበኩር የካቲት 16/2012
Next articleየወደብ ግንባታውን ተከትሎ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡