220 ሺህ የቤተሰብ አባላት በአነስተኛ መዋጮ የጤና መድኅን ተጠቃሚ መኾናቸውን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ።

17

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የ2016 ዓ.ም ጤና መድኅን ሥራዎችን አስመልክቶ ከአጋሮቹ ጋር በጎንደር ከተማ መክሯል። በምክክሩ ከሁሉም የከተማ አሥተዳደሩ ጤና ተቋማት የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች፣ በየደረጃው ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች እና የቀበሌ አሥተዳደሮች የተውጣጡ አመራሮች እና የጤና መድኅን አገልግሎት ፈጻሚዎች ተሳትፈዋል።

በምክክሩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሰይድ የሻው የከተማዋን ነዋሪዎች በሕመም ወቅት ድንገት ከሚፈጠር የጤና ወጭና ጭንቀት ለማላቀቅ የጤና መድኅን አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህ ሂደት በጎንደር ከተማ ከ2013 ዓ.ም እስከ አሁን 51ሺህ 963 አባወራዎች እና 220 ሺህ የቤተሰብ አባላት በአነስተኛ መዋጮ የጤና መድኅን ተጠቃሚ መኾናቸውን አሳውቀዋል።ከዚህም ውስጥ 134 ሺህ አባላትና ቤተሰቦቻቸው የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ነው ኀላፊው ያሳወቁት።

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ዜጎች በአነስተኛ መዋጮ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ በከተማ አሥተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን አንስተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ለሕዝቡ የተሟላ የጤና መድኅን አገልግሎት ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻዎች በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በምክክሩ በታቀደው ልክ የጤና መድኅን አባል አለማፍራት፣ በስፖንሰር ስም የተሰበሰበን ገንዘብ በአግባቡ ለታለመው ዓላማ እንዲውል አለማድረግ፣ ክፍለ ከተሞች እና የቀበሌ አሥተዳደሮች ተመሳሳይ የመፈጸም ደረጃ ላይ አለመድረስ የሚታዩ ችግሮች መኾናቸው ተነስቷል። የተነሱ ችግሮችን ለመፍታትም ከተማ አሥተዳደሩ በቀጣይ ወራት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ተጠቁሟል።

የምክክሩ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ፈጣን እና ተአማኒነት ያለው የጤና መድኅን አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።በተለይም በምክክሩ የተነሱ ክፍተቶችን እንደ ተቋማቸው ተጨባጭ ሁኔታ ወስደው ለማስተካከል እና ለመፈጸም ዝግጁ መኾናቸውን አሳውቀዋል።

ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከምግብና ሥርዓተ ምግብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሀገራችን ያልተሻገረችው ትልቅ ስብራት ነው” አቶ ደመቀ መኮንን
Next articleየተከሰተውን “ጉንፋን መሰል” ሕመም እንዴት መከላከል ይቻላል?