
እንጅባራ: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ሂውማን ብሪጅ ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የሕክምና ቁሳቁስ ለእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አድርጓል።
የህክምና ቁሶቹ ለሆስፒታሉ ተገልጋዮች የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ መኾኑን ሆስፒታሉ አስታውቋል።
ድጋፉን የዩኒቨርሲቲው ምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንዴ ብርሀን በሆስፒታሉ ተገኝተው አስረክበዋል።
የህክምና ቁሳቁስ ድጋፉ ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ ኅብረተሰቡን ለማገልገል ካለው ተልእኮ አንፃር የተደረገ መኾኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
እንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል የዩኒቨርሲቲው የህክምና ተማሪዎች የተግባር ትምህርት መማሪያ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የተደረገው ድጋፍ ለሆስፒታሉ ተገልጋዮች ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር ለተማሪዎቹ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል እንደኾነ ገልጸዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አዋሳኝ ዞኖችን ጨምሮ አገልግሎት የሚሰጡ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ተጨማሪ የህክምና ቁሶችን በመጓጓዝ ላይ መኾናቸውንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል።
የሆስፒታሉ ሥራ አሥኪያጅ ደረጀ ሀይሉ ድጋፉ ለሆስፒታሉ ተገልጋዮች የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መኾኑን ተናግረዋል።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን እና የእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር አብርሃም አማረ ድጋፉ የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያስችል እና የተገልጋዮችን እንግልት የሚቀንስ ነው ብለዋል።
ሁለት አልትራ ሳውንድ ማሽኖች፣ ከ30 በላይ የህሙማን አልጋዎች፣ የቀዶ ህክምና ጠረጴዛዎች እና ሌሎችም ለሆስፒታሉ ድጋፍ ከተደረጉ የህክምና ቁሶች መካከል ይገኙበታል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!