በሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ ትግበራ ሕጻናትን ከመቀንጨር እና ከሞት መታደግ እንደተቻለ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

18

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰቆጣ ቃልኪዳን የ2015 ዓ.ም አፈጻጸም ግምገማ፣ የ2016 ዓ.ም ዕቅድ ማጽደቂያ፣ የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ማስተዋወቂያ የከፍተኛ አመራር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና አይ ኤፍ ፒ አር አይ በጋራ በመኾን ባካሄዱት የተጽዕኖ ግምገማ ጥናት የሰቆጣ ቃልኪዳን ትግበራ የማስፋፋት ምዕራፍ ትግበራ በመጀመሪያው ዓመት ሕጻናትን ከመቀንጨር እና ከሞት መታደግ ችሏል፡፡

በተጽዕኖ ግምገማ ጥናቱ ላይ በ2014 ዓ.ም ብቻ 59 ሺህ 717 ሕጻናት ከመቀንጨር እንዲሁም 2ሺህ 904 ልጆችን ከሞት መታደግ እንደተቻለ ነው የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር የገለጸው።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን የሙከራ ምዕራፍ ትግበራ በ40 ወረዳዎች የነበረውን ከ2014 ዓ.ም ጅማሮ ወደ 240 ወረዳዎች በማስፋት እየተተገበረ ይገኛል።

በኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የምግብ እጥረት እና የሥርዓተ ምግብን ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ ቢኾንም አሁንም ችግሩ አሳሳቢ መኾኑን አንስተዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ5 ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናት ወደ 39 በመቶ የመቀንጨር እና 11 በመቶ ደግሞ የመቀጨጭ ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም የሰቆጣ ቃልኪዳን እገዛ እያደረገ እንደኾነ ነው ያስረዱት።

የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) የምግብ እጥረት እና የሥርዓተ ምግብ ችግር በልጆች አስተዳደግ ብሎም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ሁላችንም ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።

የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ መጨረሻ 700 ወረዳዎችን ለማድረስ ያለመ ነው።

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥምቀትን በጎንደር ሃይማኖታዊ መሰረቱን እና ድምቀቱን በጠበቀ መንገድ እንዲከበር ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው” አቶ ጣሂር ሙሐመድ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት ለሚያከብሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።