“ጥምቀትን በጎንደር ሃይማኖታዊ መሰረቱን እና ድምቀቱን በጠበቀ መንገድ እንዲከበር ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው” አቶ ጣሂር ሙሐመድ

30

ጎንደር: ታኅሳሥ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር ቅጥር ግቢ ውስጥ የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል። የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ነዋሪዎች ጥምቀተ ባሕሩን በማጽዳቱ ሥራ ተሳትፈዋል።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሐመድ ጥምቀትን በጎንደር በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ኮሚቴ ተቋቁሞ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ስለመደረጉም ጠቅሰዋል።

ቢሮ ኀላፊው እንዳሉት የአውሮፕላን ጉዞ ለሚጠቀሙ ቱሪስቶች በርካታ የበረራ ቁጥር እንዲመደብ ከወዲሁ እየተሠራ ነው። “ጥምቀትን በጎንደር ሃይማኖታዊ መሰረቱን እና ድምቀቱን በጠበቀ መንገድ እንዲከበር ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

እንግዶች በፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር የተሟላ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ የክልሉን የሀገር ውስጥ የጎብኚ ፍስሰት ለመጨመር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የተለያዩ ተቋማትን ያሳተፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑ አንስተዋል።

በዓሉን ተከትሎ በእንግዶች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ እንዳይደረግም ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ከባለሃብቶች ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል። “ጎንደር እንግዷቿን ለመቀበል እየተሰናዳች ነው” ሲሉም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ታኅሳስ 22/2016 ዓ.ም ዕትም
Next articleበሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ ትግበራ ሕጻናትን ከመቀንጨር እና ከሞት መታደግ እንደተቻለ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።