
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያለመ ሕዝባዊ ውይይት ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደና የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጀነራል ዘውዱ በላይ በተገኙበት በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ መንግሥት ያቀረበዉን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሳቸው ተገልጿል።
የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ጥያቄዎቹን በትጥቅ ትግል ለመፍታት ሲንቀሳቀስ የነበረውና ራሱን የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) ብሎ የሚጠራው ኀይል ወደ ሰላማዊ ትግል ለመመለስ በመወሰን የክልሉ መንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሏል።
የአዴን አባላት የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲመለሱ እንደሚደረግና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ምቹ መደላድል እንዳለም ተገልጿል።
ጥያቄዎችን በግጭትና በጦርነት ለመፍታት የሚደረግ እንቅስቃሴ ብሔረሰብ አሥተዳድሩንም ኾነ ክልሉን ዋጋ የሚያስከፍል በመኾኑ የሰላም ስምምነቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጠቀሜታው የጎላ መኾኑን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳድሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኀይሉ ግርማይ የሰላም ስምምነቱ የሕዝቡን የሰላም ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ የዋግን ሕዝብ የሰላም አምባሳደርነት ባሕል ያሳየና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚፈታ ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም መመለሳቸው ለአካባቢው ዘላቂ ፀጥታ ሚናው የጎላ ነው፤ ለውጤታማነቱ ሕዝቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግና የተመለሱ ኀይሎችንም ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የዋግን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተደረገው ስምምነት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥትም የዋግን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!