
ደብረ ብርሃን: ታኅሳሥ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ የ2015 በጀት ዓመት የጤና መድኅን አፈጻጸም ግምገማ እና ስለ2016 በጀት ዓመት የሥራ አቅጣጫዎች ውይይት እያካሄደ ነው።
የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ጸዳለ ሰሙንጉሥ የዞኑን ማኅበረሰብ ጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል። ዞኑ ባለፈው ዓመት 362 ሺህ 950 እማወራ እና አባ ወራዎችን የጤና መድኅን ተጠቃሚ በማድረግ የተሻለ ተሞክሮ እንዳለው ተናግረዋል። በዚህ ዓመትም እሰከ የካቲት 15/2016 በነባር እና በአዲስ 419 ሺህ 600 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የምዝገባ እና የእድሳት ሥራ ይጠናቀቃል ብለዋል ።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን በየጊዜው እየገመገምን እያስተካከልን ነው ሲሉም ኀላፊዋ ተናግረዋል። በተለይም ከመድኃኒት አቅርቦት እና የኪስ ትክ ክፍያ ችግርን ለመፍታት የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤቶችን በወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች መከፈት እንደሚያስፈልግ ሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማኅበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኀን ተጠቃሚ እዲኾኑ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። በ2015 በጀት ዓመት በክልሉ የጤና መድኅን አባል ከነበረው ከ17 ነጥብ 8 ሚሊዮን የቤተሰብ አባል 14 ነጥብ 8 ሚሊየኑም በጤና ተቋም የሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል ብለዋል።
የጤና ተቋማት ሥራ በጸጥታ ችግር ወቅት መቋረጥ ሳይሆን የበለጠ መጠንከር የሚገባው በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ኀላፊነት የተሞላበት ሥራ መሥራትም ይጠበቃል ተብሏል።
ዘጋቢ:- ለአለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!