ነገ በሚጀመረው የተጫዋቾች ዝውውር ክለቦች ተጫዋቾችን ለማስፈረም ድርድራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

40

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ የእግር ኳስ ቡድኖች እ.ኤ.አ ጥር 1/2024 በሚጀመረው የዝውውር ጊዜ በርካታ ተጫዋቾችን በክፍያ፣ በነጻ እና በውሰት ለማስፈረም መዘጋጀታቸውን እየጠቆሙ ነው፡፡

ቶትንሃም የሮማንያ ዜግነት ያለውን የጄኖአ ተከላካይ ራዱ ድራጉሲንን ለማስፈረም ጥያቄ ሊያቀርብ ነው ተብሏል፡፡

ስፖርት ኢታሊያ እንደዘገበው የ21 ዓመቱ ራዱ ድራጉሲን ወኪል ተጫዋቹ የዝውውር ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

ባርሴሎና ማሶን ግሪንውድን ለማዘዋወር እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ተጫዋቹ እ.ኤ.አ በ2018 ማንቸስተር ዩናይትድን በ40 ሚሊዮን ፓውንድ በመቀላቀል በ82 ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡

22 ግቦችንም በስሙ አስመዝግቧል፡፡ ይሁንና ክለቡ በውሰት ለስፔኑ ጌታፌ ክለብ አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡

ይህን ተጫዋች አትሌቲኮ ማድሪድም በጥብቅ እየፈለገው መኾኑን ማርካ አስነብቧል፡፡

ማንቸስተር ዩናይትዶች የ30 ዓመቱን ፈረንሳዊ ተከላካይ ራፋኤል ቫራን ለመሸጥ መዘጋጀታቸውን ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል፡፡

ብሬንትፎርድ የሪያል ቤቲሱን የክንፍ መስመር ተጫዋች አሳን ዲያኦን ለማስፈረም መዘጋጀቱ እየተነገረ ነው።

ማንቸስተር ዩናይትድ የስዊድን ተከላካዩን የቪክቶር ሊንደሎፍን ኮንትራት እስከ 2025 ለማራዘም ወስኗል፡፡

የተጫዋቹ ውል በዚህ ክረምት ወራት የሚያልቅ ይኾናል በማለት የዘገበው ማርካ ነው፡፡

በሩሲያ ዶርትሙንድ የ21 ዓመቱን ኔዘርላንዳዊ የቼልሲ ተከላካይ ኢያን ማሴን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል ተብሏል፡፡

ኖቲንግሃም ፎረስት የፍሉሚንሴውን ብራዚላዊ የመሀል ተከላካይ ኒኖን ለማስፈረም 6 ሚሊዮን ፓውንድ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም የ28 ዓመቱን ፖርቱጋላዊ የክንፍ መስመር ተጫዋች ጌልሰን ማርቲንሰንን ለማስፈረም ከሞናኮ ጋር ድርድር ላይ ናቸው ሲል ዘሚረር ዘግቧል፡፡

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሀራ ከተማ ነዋሪዎች ሰላምን በማስጠበቅና በልማት ሥራዎች ተሳትፏቸው የሚመሠገን ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን
Next articleበበጀት ዓመቱ ከ419 ሺህ በላይ የዞኑን ነዋሪዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።