
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የዕለት ተዕለት ተግባር ሊኾን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ለሀገራዊ ምክክሩ የተሳታፊ ልየታ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ከ60 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች መለየታቸው ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ለሀገራዊ ምክክርና መግባባት የኪነጥበብ፣ የማስታወቂያና የሁነት ዝግጅት ተቋማትና ባለሙያዎች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ከተቋማት ኃላፊዎች፣ ከጥበብ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ውይይት አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ.ሮ) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
የምክክሩን ዓላማ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ተቀራርቦ መሥራት ሲቻል ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን የኪነጥበብ፣ የማስታወቂያና የሁነት ዝግጅት ተቋማትና ባለሙያዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ምክክሩ የመንግሥትና የምሁራን ሀሳብ ብቻ የሚንጸባረቅበት ሳይኾን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩል ተሳትፈውበት የጋራ ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ለምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ገልጸው የምክክሩን ሂደት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
በኮሚሽኑ የሚዘጋጁትን ሁነቶችና በራሳቸው አጀንዳ እየቀረጹ ስለምክክሩ ዓላማ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ያደረጉ ተቋማትን አመሥግነዋል። የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ተጠናቅቆ ዓላማውን እውን ማድረግ እስከሚቻል ድረስ መገናኛ ብዙኃን ለምክክሩ የሚሰጡትን ሽፋን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ በተሠሩት ሥራዎች አማራና ትግራይ ክልሎችን ሳይጨምር በሌሎች አካባቢዎች ከ60 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ተለይተዋል ብለዋል ዋና ኮሚሽነሩ። በቀጣይ በክልልና በፌደራል ደረጃ ተገናኝተው አጀንዳ የሚሰበሰብበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።
ምክክሩን አሳታፊና አካታች ለማድረግ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያና በሌሎች የውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በበይነ መረብ አማካኝነት ውይይት ማድረጋቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድኅን በበኩላቸው እንደገለጹት በአማራ ክልል የተባባሪ አካላትን ለመለየት የአሠልጣኞች ሥልጠና የሚሰጡ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ማሠልጠን እንደሚጀምሩ አመልክተዋል፡፡
በትግራይ ክልልም የተለያዩ ኅብረተሰቡን ሊወክሉ የሚችሉ የሲቪክ ማኅበራትን፣ የሴቶች ፎረም፣ የአካል ጉዳቶች ማኅበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ክልል የተሳታፊና የተባባሪ አካላት ልየታ ያልተጀመረው በክልሎች ባለው የሰላም ኹኔታና በቂ የሰው ኃይል ባለመኖሩ መኾኑን አውስተዋል፡፡
የተሳታፊና ተባባሪ አካላት ልየታ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች በቅርቡ አጀንዳ ማሰባሰብ እንደሚጀመር አመልክተዋል። በሂደት ላይ የሚገኘውን ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የሀገራዊ ምክክሩ ኮሚሽነሮች፣ አርቲስቶች፣ የማስታወቂያ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።ተሳታፊዎች ሀገራዊ ምክክሩን በመደገፍ ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም በሙያ ዘርፋቸው እገዛ እንደሚያደርጉ ኢፕድ ዘግቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!