
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ግብፅ የዓባይ ግድብን በተደጋጋሚ የውዝግብ ማዕከል ለማድረግ የምታደርገው ጥረት የውኃው ብቸኛ ተጠቃሚ እና ባለቤት እኛ ነን ከሚል ፍላጎት የመነጨ መኾኑን የውኃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
የውኃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ.ር) እንደገለጹት ግብጽ በተደጋጋሚ የዓባይ ግድብን የውዝግብ ማዕከል ለማድረግ የምታደርገው ጥረት ዓባይን ጨምሮ በጠቅላላ በዓባይ ተፋሰስ ላይ በታሪክም በተፈጥሮም መብታችን ሊነካ አይችልም ከሚል መነሻ የሚመነጭ ነው ።
ግብፆች ከኢትዮጵያ ጋር የመደራደር ፍላጎት ካጡ ቆይተዋል የሚሉት ተመራማሪው የግብፆች ፍላጎት በተለይም የውኃውን ባለቤትነት ኢትዮጵያ እንድትለቅላቸው እንጂ ኢትዮጵያ ባለመብት መኾኗን እና የውኃው አመንጪ ሀገር እንደመኾኗ የራሷ የልማት ፍላጎት እንዳላት ጠፍቷቸው አይደለም ሲሉ ገልጸዋል ።
ግብፆች የሚሉት የውኃ ሙሉ ባለቤትነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ውኃ አመንጪ ሀገራት ተቀባይነት እንደሌለው እንደሚረዱ ተናግረው በ 4ኛው ዙር የተደረገውን ድርድር እንዲሁም ከዛም በፊት በነበሩ ሂደቶች ግብፆች አልተስማማንም የሚሉት እኛ የምንፈልገው ካልኾነ ሌሎችን ቢጠቅምም ባይጠቅምም ድርድሩ ይፈርሳል ከሚል ግምት መኾኑን ተናግረዋል።
የውኃ ተመራማሪው እንደሚሉት ሱዳንና ግብፅ ውኃውን ሙሉ ለሙሉ የመጠቀም ስምምነት ስላላቸው ስምምነቱን ኢትዮጵያም ሌሎች ሀገራትም እንዲያፀድቁ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የውኃ ሀብቷን ለዜጎቿ የማልማት መብት ያላት መኾኑን መገንዘብ ይገባል። የዓባይ ግድብ ሥራ እየተጠናቀቀ በመኾኑ ሌሎች ግድቦችም በዓባይ ምንጮች ላይ መሠራት አለባቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በውኃ ሀብቶች ላይ የሚሠሩ ልማቶች የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት እስካልጎዱ ድረስ መቀጠል እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። በዓባይ ግድብ ላይም እነዚህ ሀገራት እንዳይጎዱ እና ለጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉንም አስታውሰዋል።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ግብፆች መልማት የኢትዮጵያ መብት መኾኑን ተቀብለው ሲመጡ አስፈላጊ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ድርድር ማካሄድ ይቻላል። ኾኖም ድርድሩ እንዲሳካ የግብፆች ሀሳብ መለወጥን ይጠይቃል። በኢትዮጵያ በኩል ግን ምንጊዜም ለድርድር ክፍት ተደርጓል።
በቀጣይ ውኃን በጋራ የመጠቀምና የመልማት ጉዳይ ላይ ብዙ ሀሳቦች ቀርበው በድርድር ወደ ጋራ ልማት ሊያመራ ይችላል ያሉት ዶክተር ያዕቆብ ይህ ካልኾነ ግን ጊዜ የሚወስድ ሊኾን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ግብፅ በሚዲያ የምታደርገው ስም የማጥፋት ዘመቻ ትክክል እንዳልኾነ አይደልም ብለዋል። የውኃ ተመራማሪው በኢትዮጵያ በኩልም የግል እና የመንግሥትም የሚዲያ ተቋማት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም የልማት ተቋማት የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ መኾኑን በማስረዳት ረገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጨመር እንዳለበት መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!