
ደብረ ብርሃን: ታኅሳሥ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ በጀት በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እየሠራ መኾኑን ገልጿል።
እነዚህን የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት የመግዛት አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራም ነው ያስታወቀው። የኑሮ ውድነትን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመከላከል ዛሬ በደብረብርሃን ከተማ የንቅናቄ መድረክ ተዘጋጅቷል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) እንዳሉት የንቅናቄ መድረኩ ዓላማ በተደራጀ አቅም ሸማች ተኮር የግብይት ሥርዓትን በመገንባት የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ነው። ሸማችን መሰረት ያደረገ ሰላማዊ ግብይት መምራት ታሳቢ ያደረገ ውይይት መኾኑም ተገልጿል።
ሸማች ተኮር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ዘመናዊና ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት መገንባት፣ በግብይት ሰንሰለቱ ያሉ ተዋናዮች በአደረጃጀት፣ በካፒታል እና ሌሎች ዘርፎች እንዲያድጉ ማስቻል፣ ሸማች እና አምራችን ማገናኘት እንዲሁም አቅም በመገንባት ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።
የታወቀ የንግድ ሥራን በመከተል ሕገ ወጥ የንግድ ተዋናዮች የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ማስቀረትም የንቅናቄ መድረኩ ዓላማ ነው።
በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተዘዋዋሪ በጀት በማቅረብ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት የመግዛት አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ ይሠራልም ብለዋል ቢሮ ኀላፊው በሰጡት ማብራሪያ።
በ77 ከተሞች እንደየ አቅማቸው አዳዲስ የገበያ ማዕከላትን በማቋቋም እና በመሥራት አምራች እንዲሁም ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘትም ይሠራል ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም እንደየኀላፊነታቸው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በትኩረት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
ከሰሜን ሸዋ ዞን እና ከደብረብርሃን ከተማ እንዲሁም ከሁሉም በዞኑ ከሚገኙ የከተማ አሥተዳደሮች ተወካይ፣ አስመጪና ላኪ፣ የምግብ አምራቾች፣ ጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች፣ ዩኒየኖች እና የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!