የታጠቁ ኀይሎች በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉበትን የፖለቲካ አውድ መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ ገለጸ።

63

አዲስ አበባ: ታኅሳሥ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሰጠው መግለጫ የተሳሳቱ መረጃዎች በማኅበረሰቡ ላይ ካለው ዓለም አቀፋዊ የሚዲያ ተደራሽነት እና አጀንዳ ፈጠራ አንፃር ተዳምሮ ማኅበረሰቡን ውዥንብር ውስጥ ከትቷል ብሏል። ይህም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ገትቷል ነው ያለው።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) እንዳሉት ይህን ለመግታት ወንድማማችነት እና ፍትሕን መሰረት አድርጎ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማት በመገንባት ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል መሰረታዊ ሰላማዊ የመታገያ ሜዳ እያለ በኀይል ነፍጥ ያነሱ አካላትን ችግር ለመፍታት መንግሥት ረጅም ርቀት እንደሄደም አስረድተዋል። የአማራ ክልልን ከሰላም እጦት በመታደግ ሰላማዊ ክልል መፍጠር ስለመቻሉም አብራርተዋል፡፡ በመኾኑም ነፍጥ ያነገቡ አካላት በሰላማዊ መንገድ መታገል የሚችሉበት ፖለቲካዊ አውድ ስለመፈጠሩም አስረድተዋል። የሰላም ጥሪም ተደርጎ ወደ ተሃድሶ የማስገባት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡ የአማራ ክልል ከሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የተለየ ጥያቄ የለውም ያሉት ሚኒስትሩ ጥያቄዎቹን ለይቶ መንግሥት እየሠራ ነው ብለዋል።

የአመራር ሥልጠናን በተመለከተ 54 ሺህ መሪዎችን መንግሥት ባለፉት 2 ወራት በቂ ሥልጠና ስለመስጠቱ ነው ያብራሩት። ሥልጠናውም የሀገር ግንባታ፣ የሃብት ፈጠራ፣ የሰላም እና ደኅንነት፣ የአካባቢያዊ እና ቀጣናዊ ሁነትን መገንዘብ እንዲችሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ሰብዓዊ እርዳታ ላይ በሀገሪቱ በተከሰተ ድርቅ በተለያዩ ክልሎች 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ለአስቸኳይ እርዳታ ጠያቂነት እንደዳረገም ገልጸዋል፡፡ በጎርፍ ምክንያት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የዚሁ ድጋፍ ፈላጊዎች ኾነዋል ነው ያሉት። በዚህም መንግሥት ከአጋር አካላት 15 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የእህል ድጋፍ ለዜጎቹ እያደረገ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።

መንግሥት ባደረገው ግምገማ ድርቁ ወደ ረሃብ ተሸጋግሯል በሚል የሚሰራጨው ፕሮፖጋንዳ ሐሰት ስለመኾኑም አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመንገድ ግንባታዎቹ የወልድያ ከተማ ሕዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልሱና ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን
Next article“የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በ77 ከተሞች አዳዲስ የገበያ ማዕከላትን በማቋቋም አምራችና ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘት እየሠራን ነው” ዶክተር ኢብራሂም ሙሐመድ