
ባሕር ዳር፡ የካቲት 15/2012 ዓ.ም (አብመድ) በቀድሞው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ስም የተሰየመው የበሽሎ ድልድይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።
የበሽሎ ድልድይ በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳን እና በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳን ያገናኛል። ድልድዩ 156 ሜትር ርዝመት ያለው ነው፤ 38 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትም ተገልጧል። የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ ለአብመድ እንደገለጹት ወጪው ሙሉ በሙሉ በክልሉ መንግሥት የተሸፈነ ነው።
ድልድዩ የሁለቱን ወረዳ ነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄ የመለሰ እንደሆነ በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ የየአካባቢዎቹ ተወካዮች መናገራቸው ታውቋል። የአርብ ገበያ-በሽሎ-ማሻ የጠጠር መንገድ በቶሎ እንዲጠናቀቅ ያሳሰቡት ነዋሪዎቹ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያለበት መሆኑን በመረዳት ወደ አስፓልት ደረጃ ማደግ እንዳለበትም ጠይቀዋል።
የአርብ ገበያ-በሽሎ-ማሻ የጠጠር መንገድ በአማራ ገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ነው እየተገነባ ያለው። አጠቃላይ ርዝመቱም 140 ኪሎ ሜትር መሆኑን አቶ ደሳለኝ ገልፀዋል። ድልድዩም በዚህ መንገድ መካከል ነው የተገነባው።
ከዚህ ውስጥ 68 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመጀመሪያው ምዕራፍ (የአርብ ገበያ-በሽሎ ወንዝ) መንገድ ሥራ መጠናቀቁን የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው ከበሽሎ ወንዝ-ማሻ ያለውን የሁለተኛ ምዕራፍ ሥራ በቶሎ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የመንገዱ ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑም ወደ አስፓልት ደረጃ ለማሳደግ በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በዕቅድ እንደሚካተት የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ ገልፀዋል።
የበሽሎ ወንዝ ድልድይ ለቀድሞው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን መታሰቢያ እንዲሆን በስማቸው ተሰይሟል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ ሌሎች የፌዴራልና የክልል፣ የሁለቱም ዞኖች እና ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል።
ዘጋቢ:- አስማማው በቀለ
ፎቶ፦ ከታች ጋይንት ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን