“የመንገድ ግንባታዎቹ የወልድያ ከተማ ሕዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልሱና ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን

19
ደሴ: ታኅሳሥ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በወልድያ ከተማ በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘውን የመንገድ ግንባታ የሥራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል። ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ግንባታዎች የወልድያ ከተማ ሕዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልሱ፣ ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል።
የግንባታ ሥራዎቹ በጥሩ ሂደት ላይ መኾናቸውን እንደተመለከቱ ገልጸዋል። የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች በሰላም ማስፈን ሥራ እና በልማት ሥራዎች ላይ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አመሥግነዋል፡፡
የገንዘብ እጥረቱን ለመፍታት ከተማ አሥተዳደሩ ከሚያቀርባቸው አማራጮች ባሻገር ከባንኮች ለሚወስደው ብድር የክልሉ መንግሥት ዋስትና በማቅረብ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል። በመንገድ ሥራው የሥራ እንቅስቃሴ ምልከታ ላይ የወልድያ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዓለምነው ጌጡ ከተማ አሥተዳደሩ ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን የተጀመሩ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ለመንገድ ግንባታው የገንዘብ እጥረት ፈተና እንደኾነበት ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል። በከተማ አሥተዳደሩ በጀት እየተገነቡ ለሚገኙ የመንገድ፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማስፋፊያ እና ለሌሎች ሥራዎች በጥሬ ገንዘብ ብቻ 12 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና ወንድማማችነት የዳበረ ነው” አቶ ደመቀ መኮንን
Next articleየታጠቁ ኀይሎች በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉበትን የፖለቲካ አውድ መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ ገለጸ።