
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአሁናዊው የሱዳን ፈተና ኢትዮጵያ ከሱዳን ሕዝብ ጎን እንደምትቆም ገልጸዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን የሱዳን ሪፐብሊክ አምባሳደር ጀማል አል ሼይክን አሰናብተዋል፡፡
“የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና ወንድማማችነት የዳበረ ነው” ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን አምባሳደር ጀማል ይህ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ላደረጉት ከፍ ያለ ጥረት እና አስተዋጽኦም ምስጋና አቀርበዋል፡፡ የሱዳን አንድነት ተጠብቆ ሱዳናውያን በሚያምኑበት የሠላም ሂደት አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ እና ዘላቂ ሠላም በሱዳን ማስፍን አስፈላጊ እንደኾነም አንስተዋል።
አምባሳደር ጀማል አል ሼይክ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሀገራቸው እንደኾነች እና በሥራ ዘመናቸው ከተለያዩ ተቋማት ለተደረገላቸው ከፍ ያለ ድጋፍ ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አምባሳደሩ ከሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ግጭቱ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ባሻገር በጦርነቱ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሱዳናውያን የምታደርገው ድጋፍ በሱዳናዊያን ዘንድ የማይረሳ ውለታ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!