
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከጥር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት ትምህርት ይጀምራሉ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን በቅርቡ ይጀምራሉ ብሏል።
በአማራ ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በ2016 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያዉ ወሰነ ትምህርት ተማሪዎቻቸውን ለመጥራት እና መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸዉን ሙሉ ለሙሉ መጀመር አልቻሉም ነበር።
የትምህርት ሚኒስቴር ከክልሉ ኮማንድ ፖስት፣ የጸጥታ አደረጃጀቶች እና የሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ሲያካሂድ እንደቆየ ገልጿል። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአስሩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ ፀጥታ አካላት ትናንት ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም በጉዳዩ ዙሪያ መክረዋል።
ከውይይቱ በኋላ አሁን በክልሉ አንጻራዊ ሰላም የተፈጠረ በመኾኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎችን መጥራት እና ማስተማር እንደሚችሉ ውሳኔ ላይ ተደርሷል። በዚህም ከጥር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ዩኒቨርስቲዎቹ ተማሪዎችን ጠርተው የመማር ማስተማር ሥራቸውን ይጀምራሉ ተብሏል።
በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚያደርጉትን ጥሪ እንዲከታተሉ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቁሟል፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
